1በቍጣዬ በያዝኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉና፥ ይቀሠፋሉምና ዛሬ ራሳቸውን ለሚያስታብዩ ለጢሮስና ለሲዶና፥ ለይሁዳ ሀገር አውራጃዎችም ሁሉ ወዮላቸው። 2እግዚአብሔር እንዲህ አለ፥ “ትዕቢተኛና ኵራተኛ የጥፋት ልጅ፥ የጽድቅ ጠላት አንገቱን የሚያደነድን፥ የሚመካና ፈጣሪውን የማያውቅ ከእነርሱ ይወጣልና፥ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ኀይሌን እገልጽ ዘንድ ለቍጣዬ አምሳል አደረግሁት” ብሎአልና። 3ይህቺም ቅፍርናሆም፥ ሰማርያና ገሊላ፥ ሶርያና ደማስቆ፥ ቆጵሮስና አካይያ፥ የዮርዳኖስም አውራጃ አሕዛብ ሁሉ፥ አንገታቸውን ያደነደኑ፥ በልማዳቸው የሚሄዱ፥ የሞት ጥላና ጨለማም የሸፈናቸው ናቸው፤ ዲያብሎስ ልቡናቸውን ሸፍኖታልና፥ ለዚያም ለትዕቢተኛ ይታዘዙለታልና እግዚአብሔርን ወደ መፍራት አይመለሱም። 4ለርኩሳን ለሚታዘዙላቸው፥ በስማቸውም መሥዋዕት ለሚሠዉላቸው ያንጊዜ ወዮላቸው! የፈጠራቸው እግዚአብሔርን ክደውታልና፥ አእምሮ የሌላቸው እንስሳትን ይመስላሉ፤ ያ ዝንጉ የጥፋት ልጅ በቦታው ሁሉ ምስሉን ያቆማልና በእጁ ሥራና በልቡ ፍላጎት፥ በቅሚያና በኀጢአትም ሁሉ፥ በክዳትና በበደልም፥ በቅሚያና ሰው በሚሠራው ዝሙት ሁሉ፥ በሐሰት ነገርም ደስ ይለዋል። 5ይህን እንዲሠራው በእግዚአብሔር ዘንድ የተቈጠረ ስለ ሆነ እንዲህ እንዲያደርግ በዘመኑ ይታወቃልና። 6ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ደም ትሆናለች፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በውስጥዋ በሚኖሩ ሰዎች በእጃቸው ሥራ መጠን ምድርንና በውስጧም ያለውን ሁሉ ያሳልፍ ዘንድ በኋለኛው ዘመን በሚመጣው ተአምር ሥራው ሁሉ ይጠፋል፤ 7እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረት ላይ ኰርትዋልና፥ በአንድ ሰዓትም እንደ ወደደ አድርጓልና፥ የኋለኛውን ጠላት ሞት ይሽረዋል። 8ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር “እኔ እበቀላለሁ” ብሏልና ከዚያ በኋላ ሥልጣን የለውም። 9እርሱም በቍጣዬ በተያዘበት ቀን ተጠብቆለት ወደ አለ ወደ መቅሠፍትና ወደ ፍርድም ይወርዳል፤ ከእርሱ ጋር ያሉትን ሁሉ ወደ ጥፋት፥ ወደ መከራና ወደ ክሕደት ይስባልና፥ ከገሃነም ፍርድ የማወጣና የማገባ እኔ ነኝና፥ 10እርሱ ለደከሙ ሰዎች ጽናትንና ኀይልን ይሰጣልና፥ ዳግመኛም ለኀይለኞችና ለጽኑዓን ሰዎች ድካምን ይሰጣልና ኀይለኛ በኀይሉ አይመካ። 11እርሱ እግዚአብሔር ገዢ ነውና፥ የሚበድሉትንም ሰዎች ከሚበድሏቸው ሰዎች እጅ ፈርዶ ያድናቸዋልና የባልቴቶችንና የሙት ልጆችን በቀል ይመልሳል። 12ለምትመኪ፥ አንገትሽንም ለምታደነድኚ ለአንቺ ወዮልሽ፤ በቍጣዬ የማልይዝሽና የማልበቀልሽ፥ ይመስልሻል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተነገረ፥ “በጧት የሚወጣ የአጥቢያ ኮከብ ከሰማይ ለምን ወደቀ? 13በትዕቢቱና በትምክሕቱ ዙፋኔን በሰማያትና በከዋክብት ላይ እዘረጋለሁ፤ እንደ ልዑልም እሆናለሁ” ብሏልና። 14ይኸንም በትዕቢትህ ደፍረህ ተናገርህ፤ በእጁ የፈጠረህንና የሠራህን እግዚአብሔርንም አላሰብኸውም፤ በልቡናህ ጽናት ወደ ገሃነም ትወርድ ዘንድ አንተ ራስህን ለምን ከፍ ከፍ አደረግህ? 15እንደ አንተም ከአሉ መላእክት ሁሉ በትዕቢትህ ተዋረድህ፤ እነርሱ በልብ ትሕትና ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑታልና፥ ከትእዛዙም አይወጡምና የፈጠራቸውና የሠራቸውም እርሱ እንደ ሆነ አውቀዋልና፥ ከትእዛዙም እንዳይወጡና እንዳይተላለፉ ሕሊናቸውን ጠበቁ። 16አንተ ግን በልቡናህ ትዕቢት ክፉን አደረግህ፤ ከጓደኞችህም ተለይተህ የተዋረድህ ሆንህ፤ እንደ አንተ ያሉ ኃጥኣንና ከአንተ ፍጥረት ወገን የሆኑ፥ እንደ አንተም የሚክዱ ዝንጉዎች ለሚኖሩበት ኀጢአትና በደል፥ ሽንገላና ቅሚያ ሁሉ አንተ ጠባቂው ነህና ክፋትን የምታስተምራቸው፥ በፈቃድህና በትእዛዝህ ይሔዳሉ። 17አንተና በተንኰልህ ያሳትሃቸው በአንድነት ወደ ገሃነም ትወርዳላችሁና ወዮልህ። 18በሚያስት በዚያ በወንጀለኛ የሳታችሁ የእግዚአብሔር ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እርሱና አጋንንቱ በአስተማሯችሁ እንደ እርሱ ስታችኋልና ለዘለዓለም መውጫ ወደሌለበት መቅሠፍት በአድነት ትወርዳላችሁ። 19ቀድሞም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ሳለ በኮሬብና በክርክር ውኃ፥ በደብረ ሲናና በአማሌቅ አሳዘናችሁት። 20ዳግመኛም ወደ ከነዓን ጕበኛ በላካችሁ ጊዜ ጎዳናው ሩቅ ነው፤ እስከ ሰማይ የሚደርስ ቅጽራቸውም፥ አንባቸውም ጽኑ ነው፤ አርበኞችም በዚያ ይኖራሉ ብለው ይህን በነገሩአችሁ ጊዜ የሚያስጨንቅ ሥራ ወደምትሠሩበት ወደ ግብፅ ሀገር ትመለሱ ዘንድ ተቈጥታችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ። 21ከመከራው ያዳናችሁን፥ በግብፅም ታላላቅ ተአምራትን አድርጎ በመልአኩ እጅ የመራችሁን እግዚአብሔርን አላሰባችሁትም። ፀሐይ እንዳያቃጥላችሁ ቀን በደመና ይጋርዳችሁ ነበር፥ እግራችሁም በጨለማ እንዳይሰናከል ዐምደ እሳት በሌሊት ያበራላችሁ ነበር። 22ሠራዊቱና ፈርዖንም ባስፈሯችሁ ጊዜ ፈጽማችሁ ወደ ሙሴ ጮኻችሁ፤ ሙሴም ፈጽሞ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ ከፈርዖንም ሠራዊት ጋር እንዳትገናኙ በመልአኩ ጠበቃችሁ። 23እነርሱን ግን በመከራ መለሳቸው። “እግዚአብሔር ብቻውን መራቸው፤ ከእነርሱም ጋር ሌላ አምላክ አልነበረም” ብሏልና። ጠላቶቻቸውን ግን አንድ ጊዜ በባሕር ቀበራቸው፤ ከእነርሱም የሚሸሸውን አላስቀረም። 24እስራኤልንም በባሕሩ መካከል በእግር አሻገራቸው። ከግብፃውያንም የተነሣ ያገኛቸው ክፋት ምንም የለም። ወደ ደብረ ሲናም አደረሳቸው፤ በዚያም አርባ ዘመን መናውን መገባቸው። 25የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ያሳዝኑታልና ይህን ያህል መልካምን አድርጎላቸው እግዚአብሔርን ማምለክን ቸል አሉ። 26ከልጅነታቸውም ጀምሮ እስኪያረጁ ድረስ ክፋትን በልቡናቸው አኖሩ። የእግዚአብሔር አንደበት በአበው የትውልድ መጽሐፍ እንደዚህ ብሎ ተናግሯልና፤ “የአዳም ልጆች ልቡናቸው ዐመድ ነው፤ ሥራቸውም ሁሉ ወደ ቅሚያና ወደ ክፋት መሮጥ ነው፤ ከእነርሱም በግፍ የሰውን ገንዘብ ከመሰብሰብ፥ በሐሰትም ከመማል፥ ባልንጀራውንም ከመግደል፥ ከመቀማትና ከመስረቅ በቀር የቀናች ሥራን የሚወዳት የለም። 27ሁሉም በሕይወት ዘመናቸው ወደዚህ ክፋት ይሄዳሉ፤” የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ያፈረሱ የእስራኤል ልጆችም ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ እግዚአብሔርን ፈጽመው አሳዘኑት።