1እግዚአብሔርም የቀደሙ ወገኖችን ስለ ቃየን ልጆች ኀጢአት በጥፋት ውኃ በቀጣቸው ጊዜ ምድርን በማየ አይኅ አጠመቃት፤ ከቃየን ልጆች ኀጢአትም ሁሉ አነጻት። 2“ሰውን ስለ ፈጠርሁት አዘንሁ” ብሏልና በደለኞችን ሁሉ አጠፋ። ከስምንት ሰዎችም በቀር አላስቀረም፤ ሁሉንም አጠፋ። ከዚህም በኋላ እነርሱን አባዛቸው፤ ምድርንም መሏት፤ የአባታቸው የአዳምንም ርስት ተካፈሉ። 3ኖኅ ግን እግዚአብሔር ምድርን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ እንዳያጠፋት ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የኖኅም ልጆች የሞተውንና የበከተውን እንዳይበሉ፥ ከፈጠራቸው ከእግዚአብሔርም በቀር ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩ፥ እርሱም አምላካቸው ይሆናቸው ዘንድ፥ በከንቱም አንድ ጊዜ እንዳያጠፋቸው፥ የሳተኑንና የበልጉንም ዝናም እንዳይከለክላቸው፥ ለከብቶችና ለሰዎችም በየጊዜው ምግባቸውን ይሰጣቸው ዘንድ፥ ሣሩንና የእህሉን ፍሬ፥ ተክሉንም ይሰጣቸው ዘንድ፥ እነርሱም እግዚአብሔር በሚወደው ሁሉ ሥራቸውን ያሣምሩ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ። 4ይኸንም ሥርዐት ከሰጣቸው በኋላ የእስራኤል ልጆች በክፋታቸው እግዚአብሔርን አሳዘኑት። የፈጣሪያቸውን የእግዚአብሔርን ሕግ እንዳላፈረሱ እንዳባቶቻቸው እንደ አብርሃምና እንደ ይስሐቅ፥ እንደ ያዕቆብም አልሔዱም። 5ከታናናሾቹም ጀምረው እስከ ታላላቆቹ ድረስ የእግዚአብሔርን ሕጉን ያልጠበቁ እነዚያ የእስራኤል ልጆች በሥራቸው ጠማሞች ነበሩ። 6ካህናቶቻቸውም፥ አለቆቻቸውም፥ ጸሓፊዎቻቸውም ቢሆኑ ሁሉም የእግዚአብሔርን ሕግ ያፈርሳሉ። 7ሙሴም በሕጉ መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ባዘዛቸው በችግዚአብሔር ሕግና ሥርዐት አይጸኑም። “በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ፈጣሪህ እግዚአብሔርን ውደደው፤ 8ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ ሌሎች አማልክትን አታምልክ፤ ወደ ጐልማሳ ሚስትም አትሂድ፤ ነፍስ አትግደል፤ አትስረቅም። 9በሐሰትም አትመስክር፤ የባልንጀራህንም ገንዘብ፥ ወንድምህ የገዛውንም ሁሉ አህያውንም ቢሆን፥ በሬውንም ቢሆን አትመኝ።” 10ነገር ግን ይኸን ሁሉ ካዘዛቸው በኋላ ክፉዎች የሆኑ የእስራኤል ልጆች ወደ ኀጢአትና ወደ ክዳት፥ ወደ በደልና ወደ ቅሚያ፥ ወደ ጐልማሳ ሚስትና ወደ መስረቅም፥ ወደ ሐሰትና ጣዖቶችን ወደ ማምለክ ይመለሳሉ። 11የእስራኤል ልጆች ወደ ሣር የሚሠማራ የላምን ጣዖት በመሥራት በኮሬብ እግዚአብሔርን አሳዘኑት፤ “እነሆ፥ ከግብፅ ያወጡን አማልክቶቻችን እነዚህ ናቸው” ብለው ሰገዱ። 12በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው፤ በሉ፥ ጠጡ፤ ጠገቡም፤ ሊዘፍኑም ተነሡ። 13ስለዚህ እግዚአብሔር “ከግብፅ ሀገር ከባርነት ቤት ያወጣሃቸው ወገኖችህ በደሉ፥ ሳቱም፤ የላም ምስልም ሠርተው ለጣዖቱ ሰገዱ” ብሎታልና ሙሴ ተቈጥቶ ከሲና ተራራ ወረደ። 14ሙሴም ወገኖቹን እየተቈጣቸው ከባለሟሉ ከኢያሱ ጋራ ወረደ፤ ኢያሱም በሰማ ጊዜ “እነሆ፥ በእስራኤል ሰፈር ያርበኞችን ድምፅ እሰማለሁ” አለ። 15ሙሴም ኢያሱን እንዲህ አለው “ያልፈላ የወይን ጠጅ ድምፅ እንጂ ያርበኛስ ድምፅ አይደለም።” ወርዶም ምስላቸውን ሰበረው፤ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጽሞ አደቀቀው፤ የእስራኤልም ልጆች በተራራው አጠገብ በሚጠጡት ውኃ ውስጥ ጨመረው። 16ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስለ አደረጉ እርስ በርሳቸው ይጋደሉ ዘንድ ሌዋውያንን አዘዛቸው። 17ራሳቸውን ከመግደል፥ ዘመዶቻቸውንና አባቶቻቸውንም ከመግደል እግዚአብሔርን መገዳደር እንደሚበልጥ ዐውቀው እንዳዘዛቸው አደረጉ። 18ስለዚህም ሙሴ እንዲህ አላቸው፥ “የመገባችሁንና የተከባከባችሁን፥ ከአገዛዝም ቤት የአወጣችሁን፥ ለእነርሱና ከእነርሱ በኋላ ለልጆቻቸው ይሰጣቸው ዘንድ ላባቶቻችሁ የማለላቸው ርስትንም ያወረሳችሁ እግዚአብሔርን ስላሳዘናችሁት በእጃችሁ እግዚአብሔርን ደስ አሰኛችሁት።” 19ከዚያም ወደ ኀጢአትና ወደ ክፉ ነገር ይሄዳሉና እግዚአብሔርን ማሳዘንን አልተዉም። 20ከሕፃንነታቸው ጀምረው እስከ ጐልማሳነታቸውና እስከ እርጅናቸው ድረስ በምድር ላይ ያለውን፥ በሰማይም ለሚወዱት ያዘጋጀውን ይሰጣቸው ዘንድ በበጎ ሥራቸው እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኙት እንዳባቶቻቸው እንደ አብርሃምና እንደ ይስሐቅ እንደ ያዕቆብም አይደሉም፤ በዚህም ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድረ ርስትን፥ በወዲያውም ዓለም ለጻድቃን የተዘጋጀች የደስታ ገነትን፥ ዐይን ያላየውን፥ ጆሮም ያልሰማውን፥ በሰው ልቡናም ያልታሰበውን፥ እግዚአብሔርን በሕይወታቸው ደስ ላሰኙት ለሚወዱት ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እግዚአብሔር ያዘጋጀውን ይሰጣቸው ዘንድ፤ 21ከሓድያንና ክፉዎች በልቡናቸው ፈቃድ የሚኖሩ የእነርሱ ልጆች ግን የመገባቸውንና የተከባከባቸውን፥ ከሕፃንነታቸውም ጀምሮ የጠበቃቸውን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰሙም። 22ከግብፅ ምድር ያወጣቸውንና ከጡብ ሥራ፥ ከመራራ አገዛዝም ያዳናቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም። 23እነርሱ ግን እጅግ አሳዘኑት፤ እርሱም በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብን ያስነሣባቸው ነበር፤ እነርሱም በጠላትነት እየተነሡ እንደ ወደዱ ያስገብሯቸው ነበር።