1ያንጊዜም የምድያም ሰዎች በጠላትነት ተነሡባቸው፤ እስራኤልንም ይወጓቸው ዘንድ ሠራዊቶቻቸውን አስነሡባቸው፤ የንጉሣቸውም ስሙ አክራንድዮስ ይባላል፤ የሶርያንና የኪልቅያን፥ የደማስቆንም ብዙ ሠራዊት በጧት ሰበሰበ። 2በዮርዳኖስም ማዶ ሰፈረ፤ እንዲህም ብሎ ወደ እስራኤል መልእክተኞችን ላከ፥ “ግብር ገብሩልኝ፤ ያለዚያ ግን እቀጣችሁ ዘንድ፥ ከብቶቻችሁንም እማርክ ዘንድ፥ ንብረታችሁንም ሁሉ እወስድ ዘንድ፥ ልጆቻችሁንም እማርክ ዘንድ መጣሁ። 3ወደማታውቁትም ሀገር ማርኬ እወስዳችኋለሁ፤ በዚያም ውኃ ቀጂዎችንና እንጨት ለቃሚዎችን አደርጋችኋለሁ። 4እኛ የእግዚአብሔር ወገኖች ነን፤ የሚችለንም የለም እያላችሁ አትመኩ፤ አጠፋችሁ ዘንድ፥ ገንዘባችሁንም እዘርፍ ዘንድ እግዚአብሔር የላከኝ አይደለሁምን? የእናንተ የሆነውንም ሁሉ እሰበስብ ዘንድ ላከኝ። 5እኔ የቀጣኋቸውን ሌሎች ወገኖች በውኑ ልዩ ጣዖቶቻቸው ያዳኗቸው ማዳን አለን? ገንዘባቸውንና ጥሪታቸውን ማረክሁ፤ እነርሱንም ገደልሁ፥ ልጆቻቸውንም ማረክሁ። 6እንደዚሁም አንደ አዘዝኋችሁ ግብር ካላገባችሁልኝ እናንተንም እንደ እነርሱ አደርጋችኋለሁ።” ከብቶቻቸውንና ገንዘባቸውንም ይዘርፍ፥ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውንም ይማርክ ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻገረ። 7ከዚህም በኋላ የእስራኤል ልጆች ወደ እግዚአብሔር መራራ ልቅሶን አለቀሱ፤ ፈጽመውም ጮኹ፤ ነገር ግን የሚረዳቸው አጡ። 8ስለዚህም ለሦስቱ ወንድማማቾች እግዚአብሔር ጽናትን ሰጣቸው፤ ስማቸውም እንደዚህ ነው፤ መብክዩስ፥ መቃቢስና ይሁዳ ናቸው። መልካቸው ያማረ፥ በኀይላቸውም ሁሉ አርበኞች ነበሩ። 9የእስራኤልም ልጆች ፈጽመው ሲያለቅሱ በሰሙ ጊዜ ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጩኸት የተነሣ ልቡናቸውን አሳዘናቸው፤ ባልቴቶችና የሙት ልጆች፥ ካህናቶቻቸውና መሳፍንቶቻቸው፥ የእስራኤል ወገን ሁሉ፥ ሴቶችና ወንዶች ልጆችም ሁሉ በራሳቸው ላይ ዐመድ ነስንሰው ያለቅሱ ነበር፤ መኳንንቶቻቸውም ማቅ ለብሰው ነበር። 10መልከ መልካምና ደመ ግቡ የሆኑ እነዚያ ወንድማማቾች ግን ሔደው ያድኗቸው ዘንድ ተስማሙ፤ “ሔደን ስለ እነዚህ ሰዎች ሰውነታችንን ለሞት እንስጥ” ብለው ተማከሩ። 11አይዞህ! አይዞህ! ተባብለው፥ በወገባቸው ሰይፋቸውን ታጥቀው፥ በእጃቸውም ጦራቸውን ይዘው ሔዱ፤ አርበኛውንም ይዋጉት ዘንድ ተዘጋጅተው ሔዱ። 12በማዕድም ተቀምጦ ሳለ ደረሱ፤ መብክዩስም አርበኛውን ወጋው፤ ያላመጠውን ሳይውጠው በአንዲት አመታት አንገቱን ቈረጠው፤ ይሁዳና መቃብዩስም በንጉሡ ግራና ቀኝ የነበሩትን በሰይፍ መትዋቸው። 13ንጉሣቸውም በወደቀ ጊዜ ሁሉም ሸሹ፤ ጦሮቻቸውም በባልንጀሮቻቸው ልብ ገቡ፤ ቀስቶቻቸውም ተሰባበሩ፤ እነርሱም ድል ተነሡ። 14መልከ መልካምና ደመ ግቡ የሆኑ እነዚያ ወንድማማቾች ግን ዳኑ፤ ያገኛቸውም ምንም ክፉ ነገር የለም፤ እግዚአብሔርም መቅሠፍቱን ወደ እነርሱ መልሶታልና እነዚያ ክፉዎች እርስ በርሳቸው ተላለቁ። 15ድል ተነሡ፤ ሞቱም፤ ዮርዳኖስንም እስኪሻገሩ ድረስ ገንዘባቸውን ሁሉ ጣሉ፤ የእነርሱ የሆነውም ሁሉ ቀረ፤ የእስራኤልም ልጆች እነዚያ እንደ ሸሹና ወደ ሰፈራቸው እንደ ሄዱ ባዩ ጊዜ የዘረፉትን ገንዘብ ለራሳቸው ወሰዱ። 16እግዚአብሔርም በመብክዩስና በወንድሞቹ እጅ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ አዳናቸው። 17የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን ደስ እያሰኙት ጥቂት ወራት ኖሩ። 18ከዚያ በኋላ ግን ዳግመኛ ወደ ክፋታቸው ተመለሱ፤ የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔርን በሚገባ ማምለክን ቸል አሉ። 19እርሱ ግን ዳግመኛ በማያውቋቸው፥ የእርሻቸውን አዝመራ በሚሰበስቡና የወይናቸውን ተክል በሚያጠፉ፥ መንጋቸውንም በሚዘርፉና ከብቶቻቸውን በፊታቸው አርደው በማያበሏቸው፥ 20ሚስቶቻቸውን፥ ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን በሚማርኩ ወገኖች አሳዘናቸው። ሁልጊዜም እግዚአብሔርን የሚያሳዝኑት ስለ ሆነ እነርሱ ሕጉን ያፈረሱ ወገኖች ናቸውና ልጆቻቸውን በፊታቸው ራስ ራሳቸውን ይቀጠቅጧቸዋል፤ ሊያድኗቸውም አይችሉም።