1የጢሮስና የሲዶና ሕዝብ በባሕሩ ዳርቻና በዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ፥ በገለዓድና በካራን፥ በከናኔዎንና በኢያቡሴዎን፥ በጌርጌሴዎንና በኤዶም የሚኖሩ፥ የአማሌቅም ሕዝብ፥ 2አሕዛብም ሁሉ በየሀገራቸውና በየነገዳቸው፥ በየሥርዐታቸውና በየአውራጃዎቻቸው፥ በየሀገራቸውም ቋንቋ፥ ሁሉም እግዚአብሔር እንደ ወሰናቸው ይኖራሉ። 3ከእነርሱም ሥራቸው ያማረና እግዚአብሔርን የሚያውቁት አሉ። 4ከእነርሱም ሥራቸው ክፉ የሆነ፥ የፈጠራቸው እግዚአብሔርንም የማያውቁት አሉ፤ እንደ ሥራቸውም በሶርያው ንጉሥ በአሜኔሴር እጅ ገዛቸው፤ 5የደማስቆን ገንዘብ ይወስዳልና፥ በግብፁ ንጉሥ ፊትም የሰማርያን ምርኮ ይካፈላልና። 6የገለዓድ ተራሮችና የጌላቡሄ ሸለቆዎች፥ ሰማርያና በይሁዳ ምድር ያለ ጳንጦስም ሁሉ፥ በዐረብ በሜድና በጳርቴ፥ በሴላውግያና በቀጶዶቅያ ተራሮች የሚኖሩ፥ 7በአውራጃቸውም የሚኖሩ፥ እግዚአብሔርንም የማያውቁና ትእዛዙን የማይጠብቁ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናቸው። 8እርሱም እንደ ሥራቸው ክፋትና እንደ እጃቸው ሥራ ይከፍላቸዋል። 9የቂሳርያ አውራጃ፥ የገለዓድና የአማሌቅ ሕዝብ፥ ጽድቅን የተመላች፥ በውስጧም የእስራኤል ቅዱስ፥ በኪሩቤል ሠረገላ ላይ የሚቀመጥ፥ እጅግ የብዙ ብዙ የሆኑ መላእክት በፊቱ የሚቆሙ የሠራዊት ጌታ የሚመሰገንባት የእግዚአብሔርን ከተማ ያጠፏት ዘንድ ተባብረዋልና።