1የኤዶምያስና የአማሌቅ ሠራዊት የሰማይና የምድር አገዛዝ በእጁ ያለ እግዚአብሔርን አያመልኩትም፤ እነርሱ በእውነት የማይሄዱ ወንጀለኞች ናቸውና ቤተ መቅደሱን መርገጥ አይፈሩም። 2ከዝሙትና ደም ከማፍሰስ አባላ የተመታውንና ሞቶ ያደረውን፥ የሚመስለውንም ሁሉ ከመብላት በቀር በፊታቸው እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤ እነዚሁም የተናቁና የረከሱ ናቸው። 3ሃይማኖትና ምግባር የላቸውም፤ በጎ ሥራን የጠሉ ናቸውና፤ እግዚአብሔርንም አያውቁትም፤ ከክፋትና ከመቀማት፥ ከረከሰ ሥራና ከሁከት ሁሉ በቀር፥ አባታቸው ሰብልያኖስ እንዳስተማራቸው ከዘፈንና ከጨዋታ በቀር የሰላምን መንገድ አያውቋትምና። 4እርሱ ከአጋንንቱ ጋር ገዝትዋቸዋልና፥ ለእየራሱ የሆነ የክፉን ሥራ ሁሉ፥ ክፋትንና ቅሚያን፥ የሌላውን ገንዘብ በዐመፅ መንጠቅንና ስርቆትን፥ ሞቶ ያደረውንና አባላ የተመታውን መብላትንና ዝሙትን ያስተምራቸዋል። 5ይህንም የሚመስለውን ሁሉ፥ ወደ ጐልማሳ ሚስት መሔድንና፥ ደም ማፍሰስን፥ ለጣዖት የተሠዋውንና ሙቶ ያደረውን መብላትን፥ የሰው ነፍስንም በዐመፅ መግደልን፥ መጠቃቀስንና ምቀኝነትን፥ ስስትንና እግዚአብሔር የማይወድደውን ክፉ ሥራን ሁሉ ያስተምራቸዋል፤ ይህንም ትምህርት ዓለሙን ሁሉ ከያዘ ከእግዚአብሔር መንገድ ያርቃቸው ዘንድ ጠላታቸው ሰብልያኖስ ያመጣላቸዋል። 6የእግዚአብሔር መንገድ ግን ትሕትናና የዋህነት፥ ባልንጀራንም መውደድና ወንድምን አለማበሳጨት፥ ከሰው ሁሉ ጋርም መፋቀርና ሰላም ነው። 7ለሰው ፊት የምታዳሉ፥ ቀማኞችንና ዐመፀኞችን፥ ነጣቂዎችንና ወደ ጐልማሳ ሚስት ሒያጆችን፥ በባልንጀራቸውም ላይ ግፍንና ክፉ ሥራ ሠሪዎችን፥ በዐመፅም ባልንጀራቸውን ይበድሉ ዘንድ የሚሸነግሉ ሰዎችን አትሁኑ። 8ይጠቃቀሳሉ፤ ራሳቸውንም ይነቀንቃሉ፤ ለክፋትም ይተነኰላሉ፤ ሰዎችንም ወደ ዘለዓለም ፍርድ ያወርዷቸው ዘንድ ለማሳት ያሟርታሉ።