1ወደ እግዚአብሔር እንደምትሄድ አስብ፤ ሁሉም በእጁ አለ፤ አንተ በሠራኸውም ሥራ ይፈርድብህ ዘንድ በፊቱ ትቆማለህ። 2ቀድሞም እኮ ክፉዎችና ትዕቢተኞች የሆኑ፥ ከእነርሱም የሚበልጥና የሚበረታ የሌለ፥ የረዓይት ልጆች እንደዚሁ ነበሩ፤ ኀይላቸውንና ቁመታቸውን፥ የክንዳቸውንም ብርታት ስለ አዩ እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም፤ እርሱም ካለመኖር ያመጣቸው ፈጣሪያቸው እንደ ሆነ አላወቁትም። 3አባቶቻቸውም መላእክት ሳሉ ከመላእክት ጋራ በሰማያት ያመሰግኑ ነበር። ፈቃዳቸውም ባሳታቸው ጊዜ ወደ ዘለዓለም የፍርድ ቅጣት ወረዱ። 4ከሰው ልጆችም ሚስቶችን አገቡ፤ ስለ ልቡናቸው ትዕቢት ያስታቸው ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ይጠብቁ እንደ ሆነ ይፈትናቸው ዘንድ እግዚአብሔር የሰው ሥጋን ፈጥሮላቸዋልና። 5እነርሱ ግን ትእዛዙን አልጠበቁም፤ እርሱም ከአባታቸው ከዲያብሎስ ጋራ ወደ ገሃነመ እሳት አወረዳቸው፤ እግዚአብሔርም እንደ ሰው የበደሉ መላእክትን ተቈጥትዋቸዋልና በእነርሱ ምክንያት የሰው ዘመኑ አነሰ። 6የአዳምንም ልጆች ከእነርሱ ጋራ ወሰዷቸው፤ በእነርሱም ቅጣት ወደ ሲዖል አወረዷቸው። 7መላእክት በቃየል ልጆች ስለ ሳቱ የሰው ዘመኑ ተቀንሶአልና፤ ጥንቱን የሰው ዘመኑ ዘጠኝ መቶ ሲሆን ወደ መቶ ሃያ ዘመን ተመለሱ። 8እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፥ “እነርሱ ሥጋውያንና ደማውያን ናቸውና መንፈሴ በእነርሱ ላይ አይኖርም።” 9ስለዚህም ዘመናችን ተቀነሰ፤ ዳግመኛም ስለ በደላችንና ስለ ኀጢአታችን ዘመናችን ከቀደሙ አባቶቻችን አንሶአልና ሕፃናት ሳሉ የሚሞቱ አሉ። 10የአባቶቻችን ዘመን ግን ትእዛዙን ስለ ጠበቁ፥ እግዚአብሔርንም ስለ አላሳዘኑት በዝቶ ነበር። 11ያስተምሯቸውም ዘንድ ሴቶች ልጆቻቸውን ገሠጹ፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ እንዳይተላለፉ ወንዶች ልጆቻቸውን ገሠጹ። 12ስለዚህም ከወንዶችና ከሴቶች ልጆቻቸው ጋራ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስላላፈረሱ በእውነት ዘመናቸው በዝቶ ነበር።