1የቃየን ልጆችም በበዙ ጊዜ በገናንና ከበሮን፥ መሰንቆንና ሳንቲን፥ ጨዋታንና ዘፈንን ሁሉ አደረጉ። 2ዳግመኛም መልከ መልካም ነበረችና ስለ እርሷ ብሎ ከገደለው ከጻድቁ ከአቤል ሚስት መልከ መልካሞችና ደመግቡዎች ሴቶች ልጆች ለቃየን ተወለዱለት፤ ወንድሙንም ከገደለው በኋላ እርሷን አገባት፤ ያችም የእርሱ ነበረች። 3እነርሱንም ይዞ ከአባቱ ተለይቶ በምዕራብ በኩል ወደ ቄፋዝ ሸለቆዎች ሔደ፤ የዚያች የመልከ መልካምዋ ልጆችም እንደ እናታቸው መልከ መልካሞች ነበሩ። 4ስለዚህም መላእክት ወደ ቃየን ልጆች ወረዱ፤ አንዲት ሰዓትም አልቈዩም፥ የመረጧቸውንም ለራሳቸው ሚስቶች አደረጉ። 5ስለዚህም ስለ ስሕተታቸው ከእነርሱ ጋራ በአንድነት ወደ ስሕተት ወስደውናልና እግዚአብሔር እኛንም፥ እነርሱንም ተቈጣን። 6ዲያብሎስም “እንደ ፈጣሪያችሁ እንደ እግዚአብሔር አማልክት ትሆናላችሁ” ብሎ ሸንግሎ አባታችን አዳምንና እናታችንን ሔዋንን ወደ እርሱ ስሕተት ወሰዳቸው። 7እነርሱ ግን በድንቍርናቸው እውነት መስሏቸው፥ ለቅዱስ ስሙ ይሰግዱና ያመሰግኑ ዘንድ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸውን የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ አፈረሱ። 8የእግዚአብሔርን ሀብት ለራሳቸው ያደረጉ እነዚያን ግን እርሱ ጌታቸው አዋረዳቸው፤ ያን ትዕቢተኛም አዋረደው። 9ዳዊት፥ “በኀጢአተኛ ትዕቢት ድሃው ይቃጠላል” ብሎ እንደ ተናገረ አባታችን አዳም በዲያብሎስ ትዕቢት በፈጣሪው በእግዚአብሔር ዘንድ በእውነተኛ ፍርድ ተፈርዶበታልና። 10እንዲሁም በቃየን ልጆች የሳቱ መላእክት ወደ ስሕተታቸው ወሰዱን። ስለዚህም እግዚአብሔር የሰጠን ዘመናችን ከአባቶቻችን ዘመን አነሰ። 11እነርሱ ግን በጎ ሥራ ሠርተው ነበር፤ ክፉም አይቀርባቸውም ነበር፤ ልቡናቸውን በእግዚአብሔር አጽንተው ነበርና፥ ካስተማሯቸው ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ እንዳይሉም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ያስተምሩ ነበርና። 12እነርሱ ግን በጎ ሥራ ቢሠሩ ለልጆቻቸው ካልነገሩና ካላስተማሯቸው የሚጠቅማቸው አልነበረም። 13ዳዊት እንደ ተናገረ፥ “ከልጆቻቸው ለሌላ ትውልድ አልሰወሩም፤ የእግዚአብሔርንም ክብር፥ ያደረገውን ኀይሉንና ተአምራቱን አስተማሩ፤ እነርሱ እንደ አስታወሱ ለልጆቻቸው ያስተምሩ ዘንድ፥ ያስተውሉና ያደርጉም ዘንድ፥ የእግዚአብሔርንም ፍርድ አደራ ይሏቸው ዘንድ፥ በሥነ ምግባራቸው እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኙት እንደ አባቶቻቸውም ትእዛዙን ይጠብቁ ዘንድ ነገሩ። 14በሕፃንነታቸው እግዚአብሔርን መፍራትንና ፍርዱን እነርሱ ከአባቶቻቸው እንደ ተማሩ፥ አባቶቻቸው አደራ ያስጠበቋቸው ትእዛዙን አልተዉም። 15ልጆቻቸውም ጠባያቸውን ያሳምሩ ዘንድ፥ ለፈጣሪያቸውም ክብርን ይሰጡ ዘንድ ከአባቶቻቸው ተማሩ፤ ሕጉን ጠብቀዋልና፥ እርሱንም ወደውታልና። 16እርሱም ጸሎታቸውን ይሰማቸዋል፤ ልመናቸውንም ቸል አይልም፤ እርሱ ግን ይቅር ባይ ነው። 17ቁጣውንም መመለስ ያበዛል፤ በመቅሠፍቱም ሁሉ አያጠፋም ነበር።”