1ወንድሞቻችን፥ አስቡ፤ እግዚአብሔር በጎ ሥራን የሚሠሩ ሰዎች ጽድቃቸውን እንደሚጠብቅ ቀድሞ የነገሩአችሁን አትርሱ። 2በምድርም ላይ ፍሬያቸውን ያበዛል፤ ስም አጠራራቸውም ለበጎ ነገር እስከ ዘለዓለም ይኖራል፤ ዘራቸውም በምድር ላይ እህልን አይቸገርም። 3ስለ እነርሱ ይከራከርላቸዋልና፥ በጠላታቸውም እጅ አይጥላቸውምና ከባላጋራዎቻቸውና ከሚጠሏቸው ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያድናቸዋል። 4ስሙንም ለሚወድዱ በመከራቸው ጊዜ ረዳት ይሆናቸዋል፤ ይጠብቃቸዋልም፤ ኀጢአታቸውንም ሁሉ ይቅር ይላቸዋል።