1ዳዊት በእግዚአብሔር ተአመነ፤ በእርሱም አምኗልና መጠጊያ ሆነው፤ ከንጉሡ ከሳዖልም እጅ አዳነው። 2ልጁ አቤሴሎምም በተነሣበት ጊዜ፥ ኢሎፍላውያንም በተነሡበት ጊዜ፥ አማሌቃውያንና ኤዶማውያን፥ ቀርኒዎናውያንም በተነሡበት ጊዜ በእርሱ አምኗልና፥ ሕጉንም ጠብቋልና ከተቃወሙት ጠላቶቹ ሁሉ እግዚአብሔር ዳዊትን አዳነው። 3ያላመኑበትን ክፉ የሆኑ ነገሥታትን ግን እግዚአብሔር አላዳናቸውም፤ ድል መንሣት ከእግዚአብሔር ነውና በጠላቶቻቸው እጅ ድል ተነሡ እንጂ። 4ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አመነ፤ ከትዕቢተኛው ከአሶራዊውም እጅ አዳነው። 5ልጁ ምናሴ ግን እምነቱን በእግዚአብሔር አላደረገምና በጠላቱ እጅ ድል ተነሣ፤ ምናሴን ድል የነሡት እነዚያ ጠላቶቹም እንደ እርሱ አልሆኑም፤ መታመኑን በእግዚአብሔር አላደረገምና፥ ፈጽሞ ያከበረውና ያገነነው እግዚአብሔርንም አልፈራውምና አስረው ወደ ሀገራቸው ወሰዱት እንጂ፤ 6ዘመኑ ይበዛ ዘንድ፥ ጠላቱንም ይከራከርለት ዘንድ በኋላና በፊትም ኀይልንና ጽንዕን ይሆነው ዘንድ በፈጣሪው በእግዚአብሔር ዘንድ መንገዱን አላሣመረምና ከሰጠው ሀብት ከለከለው። 7በብዙ ሠራዊትና በፈረሶች፥ በቀስትና በጋሻም ከመታመን በእግዚአብሔር መታመን ይሻላልና። 8በእርሱም የታመነ ሰው በሕይወት ይኖራል፤ ይከብራል፤ ፈጽሞም ከፍ ከፍ ይላል። 9እግዚአብሔር ለፊት አያዳላምና በእግዚአብሔር ያላመኑና፥ በገንዘባቸው ብዛት ያመኑ ሰዎች ግን ከሰጣቸው ጸጋና ክብር የወጡ ይሆናሉ። 10ያመኑበትን ግን ይጠብቃቸዋል፤ ዐላዋቂ የሚሉትን ሰዎች ግን ዐላዋቂዎች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔርንም ለመከተል፥ ሕጉንም ለመጠበቅ ልቡናቸውን አላስጨከኑምና በመከራቸው ጊዜና ጠላቶቻቸው በተቃወሙአቸው ጊዜ ፈጥኖ አይረዳቸውም። 11እግዚአብሔርን በመከተል ትእዛዙንና ሕጉን ለመጠበቅ ለጨከነ ግን በመከራው ጊዜ መጠጊያ ይሆነዋል። 12ጠላቱን በመግደልና የጠላቱን ከብት በመማረክ፥ የጠላቱን ሀገር ሰውም በመማረክ፥ የዘመናት ዝናምን በማዝነም፥ በቡቃያውም ፍሬ፥ ክምርንም በማግባት፥ በተክሉ ቦታው ፍሬም፥ 13በሳተኑና በበልጉም ፍሬ፥ ሣሩንና ልምላሜውን በመስጠት፥ ከእጁ በታች ያሉ ወገኖቹም ደስ ይላቸው ዘንድ የተለያዩ ፍሬዎችን በመስጠት ደስ ያሰኘዋል። 14የሌላውን ድካም ይበሉ ዘንድ፥ ከጠላታቸውም በዘረፉት ገንዘብ ይጠግቡ ዘንድ፥ እንስሳትን፥ በጎችንና ላሞችንም ይዘርፉ ዘንድ፥ የሌላውንም ማዕድ ይበሉና ይለብሱ ዘንድ፥ የጠላቶቻቸውንም ልጆች ምርኮ ይወስዱ ዘንድ ደስ ያሰኘዋል። 15እግዚአብሔርም ይህን ሁሉ ለሚወድደው ያደርግለታል፤ የሚጠላውን ግን ለጠላቱ ብዝበዛ ያደርገዋል። 16እጁንና እግሩን ያስረዋል፤ በጠላቱም እጅ ይጥለዋል፤ ለጠላቶቹም መዘባበቻ ያደርገዋል፤ የእግዚአብሔርንም ሕግ ያፈረሰ፥ ደም አፍሳሽ ሆኗልና በቤቱ ዘር ደስ አያሰኘውም። 17በፍርድም ጊዜ አይጸናም፤ ለክፉ አድራጊዎችም ክፉን በሚከፍልበት ጊዜ ክፋትን ለሚሠሩ የሥራቸውን ፍሬ ይከፍላቸዋል። 18በጎ ለሚያደርጉ ግን በጎውን ይከፍላቸውና ሰው በእጁ ይጠብቃቸው ዘንድ ከእግዚአብሔር ታዘዘ። 19እርሱም ትእዛዙን ይጠብቅ ዘንድ ታዘዘ፤ ፈቃዱንም ያደርግ፥ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ያመሰግን ዘንድ፥ በፍጥረቱ ሁሉ ላይ አገልጋይ ነውና፥ ከሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ ከሰው ብቻ በቀር የፈጣሪውን ትእዛዝ የተላለፈ የለም። 20ሁሉም ያውቁታል፤ እግዚአብሔርም በየሥርዐታቸው የሚኖሩትን ሁሉ እንዳዘዛቸው በትእዛዙና በሕጉ ይጠበቃሉ። 21ሰው ግን በአራዊትና በእንስሳ፥ በአዕዋፍም፥ በፍጥረቱም ሁሉ በአነገሠው በእግዚአብሔር ላይ ይደፋፈራል። 22በባሕር ያለውን፥ በየብስ ያለውንም ሁሉ ቢሆን የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ እግዚአብሔር ለአባታችን ለአዳም ሰጠው፤ የወደደውን ያደርግ ዘንድ፥ በምድርም እንደ እህል ይበላቸው ዘንድ፥ ይገዛቸውና ያሠራቸውም ዘንድ፥ አራዊትም ቢሆኑ፥ እንስሳትም ቢሆኑ ለሰው ይታዘዙ ዘንድ እግዚአብሔር ሰጣቸው፤ የነገሡ ሰዎችም ክብርን ለሰጣቸው ለእግዚአብሔር ይታዘዙ ዘንድ፥ ያደሉለትና ይታዘዙለት ዘንድ በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ሾማቸው። 23ከሕጉ ቢወጡ ግን እርሱ ከሰጣቸው ሀብት ይለያቸዋል፤ ሰማይንና ምድርን የሚገዛ ነውና ፈቃዱን ለሚያደርግ ይሰጠዋል። 24የወደደውን ይሾመዋል፤ የወደደውንም ይሽረዋል፤ ይገድላል፤ ያድናልም፤ ይገርፋል፤ ይቅርም ይላል። 25እንደ እርሱ ያለ ሌላ የለም፤ ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ እርሱ ጌታ ነውና የሚነቅፈው የለም፤ በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። 26ይሾማል፤ ይሽራልም፤ ይገድላል፤ ያድናልም፤ ይገርፋል፤ ይቅር ይላልም፤ ያደኸያል፤ ያበለጽጋልም። 27የሚለምኑትን ልመናቸውን ይቀበላል፤ በንጹሕ ልቡና ፈቃዱን የሚያደርጉትንም እርሱ ጸሎታቸውን ይሰማቸዋል፤ በለመኑትም ሁሉ ፈቃዳቸውን ያደርግላቸዋል። 28ታላቁንና ታናሹንም እንዲታዘዙላቸው ያደርጋል፤ በተራሮችና በኮረብቶች፥ በዋሻዎችና በጫካዎች፥ በምድር ጕድጓድም፥ በባሕርና በየብስም ውስጥ ያለው ሁሉ የእነርሱ ነው። 29የአምላካቸውንም ፈቃድ ለሚያደርጉ፥ ሁሉ የእነርሱ ነው፤ ከበረከቱም አያሳጣቸውም፤ የምስጋናቸውንም ዋጋ ይሰጣቸዋል። 30በሰማይም ለአባቶቻቸው ለአብርሃምና ለይስሐቅ፥ ለያዕቆብም፥ ከሕጉና ከትእዛዙ ላልወጡ ለዳዊትና ለሕዝቅያስ፥ ለሳሙኤልም ያዘጋጀውን ክብር ይሰጣቸዋል፤ 31ከጥንት ጀምሮ ላገለገሉት ለአባቶቻቸው ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ፥ በመንግሥቱም ደስ ይላቸው ዘንድ።