1በጎ ሥራን የሚሠሩትን ሰዎች ስም እስኪ አስብ፤ ሥራቸውንም አትዘንጋ። 2የእግዚአብሔርን ፈቃድ ላደረጉ ደጋግ ነገሥታትና መኳንንት ባዘጋጃት የብርሃን ማደሪያ ከእነርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ ስምህ እንደ ስማቸው እንዲሆን ቅና። 3ዳግመኛም እንደሚፈረድባቸው፥ ከሞቱም በኋላ በሰው ዘንድ እንደሚያሟቸው የክፉዎች ነገሥታትንና መኳንንትን ስም ዕወቅ፤ ተረዳም። 4እያዩና እየሰሙ መንገዳቸውን ለእግዚአብሔር አላሣመሩምና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከአደረጉ ከዝንጉዎችና ከከሓድያን ጋር ይፈረድባቸዋል። 5አንተም ቸርና የዋህ፥ ቅንም ሁን እንጂ እግዚአብሔር በተቈጣቸው በዝንጉዎች ጎዳና አትሒድ። 6በእውነትም ፍረድ፤ ባልቴቲቱንና የሙት ልጅን አጽድቅ፤ ከሚቀሟቸው ከኀጢአተኞች ሰዎች እጅ አድን። 7ከሚቀማው እጅ ታድነው ዘንድ ለሙቱ ልጅ እንደ አባቱ ቁምለት፤ ንስሓ ያልገቡ ኃጥኣንም በሚቀመጡበት የእሳት ባሕር እንዳትደነግጥ የሙት ልጅ እንባ በፊትህ በፈሰሰ ጊዜ ደንግጥ። 8እግርህንም ወደ ሰላም ጎዳና አቅና፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃኑ፥ ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ናትና ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም። 9የእግዚአብሔር ፊቱ ግን መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ ክፉ ሥራን ወደሚሠሩ ነው፤ በተራራና በቅጥር የሚጠጋ ወንድንም አያስቀርም። 10ቃሌን የማይጠብቁትንም እስካጠፋቸው ድረስ ፊቴን አልመልስም። የሚጠሉኝንና ቃሌን የማይጠብቁትን የምበቀል እኔ እግዚአብሔር ቀናተኛ ነኝና። 11የሚያከብሩኝንና ቃሌን የሚጠብቁትንም አከብራቸዋለሁ።