1ወንድሙ የሚወድደው መስሎት በየዋህነት የተከተለውን ወንድሙን በገደለው በቃየል መንገድ አትሒድ። 2እርሱም በሴት ቀንቶ ወንድሙን ገደለው፤ በደልንና ቅናትን፥ ክዳትንም በባልንጀራቸው ላይ የሚያደርጉ ሰዎች እንደ እርሱ ናቸው። 3በቃየል ጐዳና ሔዱ፤ በየዋሁ በአቤል መንገድም አይደለም፤ አቤል እንደ በግ የዋህ ነውና፥ ደሙም በንጹሕ ልቡና ለእግዚአብሔር እንደ ሠዉት እንደ ንጹሕ በግ ደም ነውና። በየዋሁ በአቤል መንገድ የሚሄዱ ግን እግዚአብሔርን ይወድዱታል። 4እንደ አቤል የዋሆች ሆነዋልና እግዚአብሔርም በየዋህነት የሚሄደውን ሁሉ እንደ ጻድቁና እንደ የዋሁ አቤል ይወድደዋል። 5ክፉዎችን ግን እግዚአብሔር ቸል ይላቸዋል፤ ፍርዳቸውም በአንገታቸው ላይ ይጠብቃቸዋል፤ በትከሻቸውም ላይ የተጻፈ ነው። በፍርድ ጊዜም በመላእክትና በሰዎች፥ በፍጥረቱም ሁሉ ፊት ያነቧታል። 6የዚያን ጊዜም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ያላደረጉ ከሓዲዎችና ዐመፀኞች ያፍራሉ። 7“እስከ ዘለዓለሙ ድረስ መውጫ በሌለባት በገሃነመ እሳት ጨምሩዋቸው” የሚል አስደንጋጭ ቃል ይሰጣቸዋል።