1ጌዴዎን እግዚአብሔርን በታመነው ጊዜ በጥቂት ሠራዊት እልፍና የብዙ ብዙ የሆኑ፥ እንደ አንበጣም ቍጥር የሌላቸው ያልተገረዙ የአሕዛብን ሠራዊት ድል ነሣ። 2ነገሥታትና መኳንንት ሆይ! ያለ እኔ ሌላ አምላክ የለምና ሌሎች አማልክትን አትመኑ። 3ከእናታችሁ ማኅፀን ያወጣኋችሁ፥ ያሳደግኋችሁም፥ የመገብኋችሁም፥ ያለበስኋችሁም እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝና ለምን ታመካኛላችሁ? ያለ እኔስ ሌላ አምላክን ለምን ታመልካላችሁ። 4ይኸን ሁሉ አደረግሁላችሁ፤ ምንስ ሰጣችሁኝ? እኔስ ከእናንተ ምን እሻለሁ? የነፍሳችሁን መዳን ነው እንጂ፥ በሕጌና በሥርዐቴ፥ በትእዛዜም ትሔዱ ዘንድ፥ እኔም የነፍሳችሁን ድኅነት እሰጣችሁ ዘንድ ነው እንጂ፤ 5ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፥ “ከጣዖትና ከጥንቆላ፥ ከሟርትም ራሳችሁን አድኑ።” 6በእነዚህ ይህን በሚያደርጉና በሚሰሟቸውም ላይ፥ ፈቃዳቸውን በሚያደርጉና ወዳጅም በሚሆኗቸው ላይ፥ በትእዛዛቸውም በሚሔዱ ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ይመጣባቸዋል። 7የማያውቋችሁና የማይራሩላችሁ ሕዝብ ይነሡባችኋልና፥ የፈጠራችሁ የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ካላደረጋችሁ ከነቢዩ ከሳሙኤል ጀምሮ ነቢያት እንደ ተናገሩ፥ ዳግመኛም ሕዝቅኤልና ሄኖክ እንደ ተናገሩ፥ አሳፍም እንደ ተናገረ የድካማችሁን ፍሬ ይበላሉ። 8እንዲህም አለ፥ “ክፉ ሰዎች ልብሳቸውን ለውጠው ይመጣሉ፤ ከመብላትና ከመጠጣት፥ በብርና በወርቅም ከማጌጥ፥ እግዚአብሔርም የማይወድደውን ሥራ ሁሉ ከመሥራት በቀር ሌላ ሕግ የላቸውም። 9እነርሱ ግን ወደ መብልና መጠጥ ለመሄድ የተዘጋጁ ናቸው፤ ከዕንቅልፋቸውም ከነቁ በኋላ ከጧት ጀምሮ እስከ ማታ ወደ ክፉ ሥራ ይሮጣሉ። በመንገዳቸው ጕስቍልናና ጥፋት እንጂ ለእግራቸው የሰላም ጎዳና የለውም። 10የሰላም መንገድንም አያውቋትም፤ በዐይኖቻቸውም ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤ ሃይማኖትና ምግባር የሌላቸው ጠማሞችና ክፉዎች ናቸው፤ ስስታሞች፥ በላተኞችና ጠጪዎች፥ ሰካራሞችና በደላቸውም ያለ ሕግ ነው። ወደ መዳራትና ደም ወደ ማፍሰስ ወደ ስርቆትና ወደ መክዳትም፥ በግፍም የሌላውን ገንዘብ ወደ መቀማት የሚሄዱ ናቸው። 11ያለ ፍርድና ያለ ሕግም የሚወቅሱ ናቸው፤ የፈጠራቸው እግዚአብሔርንም አይፈሩትምና በፊታቸው ሐፍረት የለም። 12የሚያዩትን የሰውን ፊት አያፍሩም፤ የሽበታምና የሽማግሌ ፊትን አያፍሩም፤ የዓለምንም ገንዘብ በሰሙ ጊዜ በዐይናቸው ሳያዩት የራሳቸው ገንዘብ ያደርጉታል፤ በዐይናቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለምና በዐይናቸው በአዩት ጊዜ ባፋቸው የበሉት ይመስላቸዋል። 13መኳንንቶቻቸውም ያደራ ገንዘብ ይበላሉ፤ እነርሱም ከዳተኞች ናቸውና፥ በአንደበታቸውም እውነት የለምና ጧት የተናገሩትን ማታ አይደግሙትም። 14የድሆችንና የጦም አዳሪዎችን ጩኸት ቸል ይላሉና፥ ስደተኞችንም ከሚቀሟቸው እጅ አያድኗቸውምና የሚያውኩ ንጉሦቻቸው ለክፋት ይፋጠናሉ። 15ስለዚህም የተበደለውንና ስደተኛውን ያድኗቸው እንጂ ነገሥታቱ ፍርድን የሚነፍጉ አይሁኑ።” 16እነርሱ ግን ግብር የሚያስገብሩ ደምንም የሚጠጡ ወንጀለኞች ናቸው፤ መንገዳቸውም ክፉ ነውና እንቦሳዪቱን ከእናትዋ ጋር፥ ወፍንም ከጫጩቶችዋ ጋር ሲበሉ አይራሩም፤ ያዩትንና የሰሙትንም ሁሉ ለየራሳቸው ያደርጋሉ። 17እነርሱ ለራሳቸው ይሰበስቡ ዘንድ ይወድዳሉ እንጂ ለሕመምተኞችና ለድሆች አይራሩም፤ በዐመፅም የሌላውን ገንዘብ ይቀማሉ፤ በቤታቸው ያደልቡ ዘንድ፥ በእርሱም ደስ ይላቸው ዘንድ ያገኙትን ሁሉ ይሰበስባሉ። 18ከጕድጓዱ እንደ ወጣ፥ ፍለጋውም እንደማይገኝ፥ ወደ ቤቱም እንደማይመለስ አሸን ፈጥነው ይጠፋሉና፥ በሕይወታቸው ሳሉ በጎ ሥራን ስላልሠሩ እግዚአብሔር በቍጣው በያዛቸው ጊዜ ለነፍሳቸው ወዮላት። 19እግዚአብሔር ቸል ባላቸው ጊዜ በአንድ ወገን እንደ አሉ አንድ ጊዜ ይጠፋሉ፤ እግዚአብሔርም ወደ ንስሓ ይመለሱ እንደ ሆነ ይታገሣቸዋል እንጂ ለማጥፋት አይቸኩልምና በጊዜው ይጠፋሉ። 20ወደ ንስሓ ባይመለሱ ግን ከእነርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በሚገባ እንዳልጠበቁ ከእነርሱ በፊት እንደ ነበሩት ቀደምት ያጠፋቸዋል። 21የሰው ሥጋ የሚበሉና የሰው ደም የሚጠጡ ናቸው፤ ወደ ኀጢኣት ለመሔድ ግፍን ይታጠቃሉና በፊታቸው ሁልጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤ ከመኝታቸው ከተነሡ በኋላ ዐመፅ ለመሥራት አያርፉም። 22በምድርም ላይ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ያጠፉ ዘንድ፥ ሥራቸው መብላትና መጠጣት፥ ወደ ክፋትና ወደ ጥፋትም መሮጥ ነው።