1መንገዳቸው ጠማማ ነውና፥ ሁሉም የሚሄዱት በሚያስተው በሰይጣን መንገድ ነውና ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር “በቍጣዬ በያዝኋት ጊዜ ለሰውነታቸው ወዮላት” ይላል። 2የእግዚአብሔርን መንገድ ግን አያውቁም፤ ወደ ኋላቸውም መልሰውታል፤ ሕጌንም ቸል ብለዋል። 3እኔም ኋላ በፍጻሜ ዘመን እንደ ሥራቸው ክፋት እከፍላቸዋለሁ። በፍርድ ቀንም የሥራቸው ክፋት በእኔ ዘንድ እንደ ተጻፈ እበቀላቸዋለሁ፤ የምገድል፥ የማድንም፥ የምገርፍ፥ ይቅር የምልም እኔ እግዚአብሔር ነኝና ከእጄ አያመልጡም። 4እኔ እግዚአብሔር ከአድማስ እስከ አድማስ ምሉ ነኝና፥ ፍጥረቱም ሁሉ በእጄ ነውና ከምድር በታችና ከሰማይ በላይ፥ በባሕርና በውኃዎችም ጥልቅ ከእጄ የሚያመልጥ የለም። 5በምድር በታች እባብን፥ በባሕርም ውስጥ ዓሣን፥ በአየርም ያሉ ወፎችን፥ በምድረ በዳም የሜዳ አህያውን አዝዛለሁ። ከአድማስ ጀምሮ እስከ አድማስ ድረስ የእኔ ነውና። 6በፊቴ ድንቅ ሥራንና ታምራትን የማደርግ እኔ ነኝና በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር ከእጄ የሚያመልጥ የለም፤ ወዴት ትሔዳለህ? ምንስ ትሠራለህ? የሚለኝም የለም። 7እኔም በመላእክት አለቆችና ሠራዊት ላይ አዝዛለሁ፤ የሚጠራው ስም ሁሉ የእኔ ነው፤ የሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ የዱር አራዊትና እንስሳትም ሁሉ የእኔ ናቸው። 8የአዜብ ነፋስ የመስዕም ሐሩር ይነሣል፤ የኤርትራ ባሕርም በኋላ ዘመን ወደ እርሷ ከሚመጣው ግርማ የተነሣ ትደረፃለች። 9እርሱ ሕያዋንንና ሙታንን ከኖባና ከሳባ፥ ከኢትዮጵያና ከሕንደኬ፥ ከአውራጃዎቻቸውና ከወሰናቸው ሁሉ ጋር ይገዛልና። 10በእጁ ባለው በትርም በየዋህነት ሁሉን ይጠብቃል፤ ብትሩም ከበትሮች ሁሉ ይበልጣልና በጎቹን በበትሩ ይጠብቃል። 11ቀንዱም ከቀንዶች ሁሉ ይበልጣል። መንግሥቱም ከመንግሥት ሁሉ ከፍ ይላል። ሥልጣኑም ዓለሙን ሁሉ የሚገዛ ነው፤ ሁሉንም የሚችል ነው፤ የሚሳነውም የለም። 12በላይ ደመናዎችን ያዝዛል፤ በታች ለእንስሳት ሣርን ያበቅላል፥ በዝርዝሩም ላይ ፍሬን ይሰጣል። 13እንደ ወደደ ለሁሉ በየወገኑ ይመግባል፤ በየፍሬውም፥ በየምግቡም የፈጠረውን ሁሉ ይመግባል፤ በምድር በታችም ለገብረ ጕንዳን፥ ለኵብኩባ፥ ከምድር በላይም ለአውሬዎችና ለእንስሳት ይመግባቸዋል፤ ለሚጸልይም ጸሎቱን ይሰጠዋል፤ የባልቴቶችንና የሙት ልጆችን ልመና ቸል አይልም። 14ይልቁንም በየጊዜው ወደ እርሱ የሚለምኑ የንጹሓንን ጸሎት ይቀበላል። የክፉ ሰዎች ወንጀላቸው እንደ ጥቅል ነፋስ፥ የበደለኞችም ጉባኤያቸው እንደ ጉም ሽንት ነውና። 15ደስታቸውም እንደምትበር ወፍ ነውና፥ የብርና የወርቅ የሚሆን የመልካቸውም ደም ግባት በምድር ጠፊ ነውና ለዝንጉዎች መመርመሪያቸው ነው እንጂ ወርቃቸው አይጠቅማቸውም፤ ልብሳቸውንም ብል ይበላዋል። 16የእህሉና የስንዴው ድልብም በትልና በነቀዝ ይበላል፤ ሁሉም ትናንትና እንዳለፈችው ቀን ያልፋል፤ ከአፍ የወጣ ቃልም እንደማይመለስ የኃጥአን ብዕላቸው እንደዚሁ ነው፤ የአማረ አኗኗራቸውም እንደሚያልፍ ጥላ ነው፤ የኃጥኣንም ብዕላቸው በእግዚአብሔር ፊት እንደ ተውሶ ልብስ ነው። 17ጻድቃን ግን ቢበለጽጉ እግዚአብሔር ቸል አይላቸውም፤ ለድሃ እየራሩ፥ የሙት ልጆችንና የችግረኞችን ፍርድ እያዳመጡ፥ ከልብሳቸውም ለተራቆቱት እያለበሱ፥ እግዚአብሔር ከሰጣቸው ከቤታቸው ጥሪት ቸል ሳይሉ ለስደተኛውና ለጦም አዳሪው ይሰጡ ዘንድ በልጽገዋልና። 18የመሃይምናንንም ፍርድ አያደሉም፤ የምንደኛውንም ደመወዝ አያሳድሩም፤ የእግዚአብሔር ነገር አፉ ሁለት እንደ ሆነ ሰይፍ እውነትና ክቡር ነውና በወራቶቻቸው ቍጥር፥ በሚዛናቸውም ልክ ዐመፅን አያደርጉም።