1“አባቱና እናቱ ለሞቱበት ልጅ እውነተኛ ፍርድ ስላልፈረዳችሁ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ይቈጣልና የእስራኤል ኀያላን ወዮላችሁ። 2ጧትና ማታ ወደ መሸተኛ ቤት የምትሔዱና የምትሰክሩ፥ ፍርድንም የምታዳሉ፥ አባትና እናት የሞቱበትን ልጅና የባልቴቷን ፍርድንም የማትሰሙ፥ በኀጢአትና በመዳራትም የምትኖሩ ወዮላችሁ።” 3እግዚአብሔር የእስራኤልን ኀያላን እንዲህ ይላቸዋል፥ “በትእዛዜ ካልሄዳችሁ፥ ቃሌንም ካልጠበቃችሁ እኔ የምወደውንም ካልወደዳችሁ ወዮላችሁ! 4እኔም መቅሠፍትንና ጥፋትን፥ መከራንም አመጣባችኋለሁ፤ ነቀዝና ብልም እንደ በላው ትጠፋላችሁ፤ ፍለጋችሁም በአውራጃዎቻችሁ አይገኝም። 5ሀገራችሁ ምድረ በዳ ትሆናለች፤ ቀድሞ ያያትም ሁሉ እጁን ያጨበጭባል፤ ይህች ሀገር በረከትንና መልካምን ሁሉ የተመላች አልነበረችምን? እግዚአብሔር፦ በሚኖሩባት ሰዎች ኀጢአት እንዲህ አደረጋትን?” እያለ በእርስዋ ይደነቃል። 6እግዚአብሔር በምድር ትቢያ እስኪያዋርዳት ድረስ ልቧን አኵርታለችና፤ ራሷንም ከፍ ከፍ አድርጋለችና፤ አንገቷንም አስረዝማለችና በውስጥዋም ስለሚኖሩት ሰዎች ትዕቢት ምድረ በዳ ሆናለችና፥ እሾህና አሜኬላም በቅሎባታልና ወዮላት። 7ሙጃንና አስተናግርንም አበቀለች፤ ምድረ በዳና በረሃም ሆነች፤ አውሬዎችም በውስጧ ይኖሩባታል። 8በውስጥዋም ለሚያልፉ የምታስፈራ ሆነች፤ የእግዚአብሔር ቍጣ ወድቆባታልና፥ ስለ ልቡናዋ ትዕቢትና ስለሚኖሩባት ሰዎችም ክፋት ከመዓቱ ጽዋዕ ጠጥታለችና።