1የመቄዶን ሰዎች፥ አትመኩ፤ አማሌቃውያንም፥ አንገታችሁን አታስግጉ፤ የሚበቀላችሁ እግዚአብሔር አለና። 2እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ብትሉ እስከ ሲኦል ትወርዳላችሁና። 3እስራኤል ቀድሞ በሞዓብና በሜዶን መንግሥት ወደ ግብፅ ሀገር በገቡ ጊዜ “ትገዳደሩት ዘንድ በእግዚአብሔር መገዳደር አይገባምና አትመኩ” አለ። 4“አንተም ይስማኤላዊ የባርያ ልጅ! ያንተ ወዳልሆነው አንገትህን ለምን ታስረዝማለህ? በምድርስ ይፈረድባት ዘንድ በተነሣ ጊዜ በፍርድ ቀን እግዚአብሔር እንደሚፈርድብህ አታስብምን? 5የዚያን ጊዜም እንደ እጅህ ሥራ ትቀበላለህ፤ ልቡናህንስ ለምን ከፍ ከፍ ታደርጋለህ? አንገትህንስ ለምን ታስረዝማለህ? ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር። 6ወገኖችህ ያልሆኑትን አንተ እንደ ተገዳደርህ እኔም አንተን እገዳደርሃለሁ፤ ክፉ ትሠራ ዘንድ የወደድኸውን ታደርጋለህና በላክሁህም ቦታ ቸል እልሃለሁ። 7እኔም በአንተ ላይ እንዲሁ አደርጋለሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። አንተም በጎ ብታደርግ፥ እኔ የምወደውንም ብትወድድ የለመንኸኝን ሁሉ እሰማሃለሁ። 8ፈቃዴንም ብታደርግ ፈቃድህን አደርጋለሁ፤ ጠላቶችህንም እቃወምልሃለሁ፤ ሥራህን፥ ዘርህንና ልጆችህንም እባርክልሃለሁ። 9የላሞችህንና የበጎችህን መንጋ እባርክልሃለሁ፤ በትእዛዜም ብትሄድ፥ እኔም የምወደውን ብታደርግ እጅህን ያኖርህበትን ሁሉ እባርካለሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። 10“ፈቃዴን ባታደርግ፥ በትእዛዜና በሕጌ ባትሔድ ግን ቀድሞ የተነገረው ይህ ሁሉ መከራ ያገኝሃል፤ በትእዛዜ አልታገሥህምና በሕጌም አልሔድህምና ሁልጊዜ ከምትመጣብህ ቍጣዬ ማምለጥ አትችልም። 11እኔ የወደድሁትንም አልወደድህምና፤ እኔም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቼ የፈጠርሁህ ሲሆን እኔን ከማመስገንና ከማምለክ ቸል ብለሃል። 12የወደድኸውን ሁሉ ታደርግ ዘንድ በበታችህ በአሉት ዘንድ ክብርንና ጌትነትን ሰጠሁህ። ትገድልና ታድን ዘንድ፥ ትሠራና ታፈርስም ዘንድ፥ ታከብርና ታዋርድም ዘንድ፥ ከፍና ዝቅም ታደርግ ዘንድ የአንተ ነበር። 13የእግዚአብሔርንም ፈቃድ ብታደርግ፥ በትእዛዙም ብትሔድ፥ በጌትነቱ ከእርሱ ጋራ ደስ ይልህ ዘንድ ቅድስት ሀገርንም ከወረሱ ሰዎች ጋር ተካፋይ ትሆን ዘንድ ይወድድሃል። 14እርሱ እንዲህ ብሏልና፦ ቢታገሡኝ ክብርንና መወደድን አወርሳቸዋለሁ፥ በቤተ መቅደሴም ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ እንደ ቍርባን መሥዋዕትም የተመረጡና የተወደዱ ይሆናሉ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር።” 15ከሞት ወደ ሕይወት ትሻገሩ ዘንድ መልካም ማድረግንና የድኅነት መንገድን ቸል አትበሉ። 16በጎ ሥራ የሚሠሩትን ግን እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ እንደ ጠበቀው እንደ ኢዮብ ባሮቹ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር በበጎው ሁሉ ይጠብቃቸዋል። 17ነገሥታቱን በገደላቸው ጊዜ እንደ አዳነው እንደ አብርሃም፥ ጣዖት ያስመልኩት ዘንድ በማታና በጧት በቀንና በሌሊት ሰውነቱን ሲያውኳት ከነበሩ፥ አብርሃም ከኖረባቸው ከከናኔዎን እጅና ከፈርዖን እጅ እንዳዳነው እንደ ሙሴም፤ 18እርሱ ግን የእነርሱ ወደ ሆኑ ጣዖታቱ ሲስቡት እንቢ እያለ ይታገሥ ነበረ። 19እርሱም እንቢ ይላቸው ነበረ፤ የፈጠረው እግዚአብሔርንም ያመልከው ነበረ። ከልጅነቱ ጀምሮ እርሱን ያመነው አብርሃም ለእግዚአብሔር የታመነ ወዳጁ ነበረና። 20እግዚአብሔርን ፈጽሞ ይወደው ነበርና እስኪሞት ድረስ እግዚአብሔርን ማምለክን አላጓደለም፤ እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ከትእዛዙ አልተላለፈም፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ ይጠብቁ ዘንድ ለልጆቹ አስተማረ። 21እነርሱም አባታቸው አብርሃም እንደ አደረገ ከአግዚአብሔር ትእዛዝ አልተላለፉም፤ “በምድር አብርሃም የሚባል ወዳጅ አለኝ” ብሎ ለመላእክት እንደ ነገራቸው እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የተናገረላቸው ባሮቹ የአብርሃም ልጆች ይስሐቅና ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ሕግ አልተላለፉም። 22“አብርሃም ወዳጄ ነው፤ ይስሐቅም ባለሟሌ ነው፤ ያዕቆብም ልቡናዬ የወደደችው ነው፤ በእነርሱም ዘንድ ተመሰገንሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር፤” 23የእስራኤልንም ልጆች ፈጽሞ ሲወድዳቸው እነርሱ ግን ዘወትር ሲያሳዝኑት ኖሩ፤ እርሱም ሲታገሣቸው፥ በምድረ በዳም መና ሲመግባቸው ኖረ። 24ልብሶቻቸውም አላረጁም፤ የዕውቀት እንጀራ መናንም ተመግበዋልና እግሮቻቸው አልነቁም። 25ልቡናቸው ግን ሁል ጊዜ ከእግዚአብሔር ይርቅ ነበር፤ ከጥንትም ጀምሮ ክፋትን የሚሠሩ ነበሩና ለመዳን ተስፋ አልነበራቸውም። 26እንደ ጠማማ ቀስትም ሆኑ እንጂ በአማረ አኗኗራቸው እግዚአብሔርን እንዳገለገሉት እንደ አባቶቻቸው እንደ አብርሃምና እንደ ይስሐቅ፥ እንደ ያዕቆብም አልሆኑም፤ በጣዖታቸው በተራራውና በኰረብታው ላይ ሁልጊዜ ያሳዝኑት ነበር፤ በተራራው ላይ፥ በዋሻውና በዛፎቹም ሥር ይበሉ ነበር። 27ፍሪዳ ያርዱ ነበር፤ መሥዋዕትም ይሠዉ ነበር፤ በእጃቸውም ሥራ ደስ ይላቸው ነበር፤ ተረፈ መሥዋዕቱንም ይበሉ ነበር፤ የመጠጡንም ቍርባን ፍላቂ ይጠጡ ነበር፤ ከአጋንንትም ጋራ ይዘፍኑና ይጫወቱ ነበር። 28አጋንንትም ጨዋታቸውንና ዘፈናቸውን ሁሉ፥ ስካራቸውንም ሁሉ ያደንቁላቸው ነበር፤ ያለልክም ዝሙትን ይሠሩ ነበር፤ እግዚአብሔር የማይወደው ቅሚያንና ስስትንም ያደርጉ ነበር። 29ለከነዓን ጣዖት ለበዓልና ለምድያም ጣዖት፥ ለኤሎፍሊ ጣዖታት ለዳጎንና ለአጵሎን፥ ለአርጤማዴስና ለሰራጵዮን፥ 30በዙሪያቸውም ላሉ ለአሕዛብም ጣዖታት ሁሉ መሥዋዕት ይሠዉ ነበር። አሕዛብም እንደሚያደርጉት በአዩትና በሰሙት ሁሉን ያመልኩ ነበር፤ አሕዛብም የሚያደርጉትን ጨዋታቸውንና ዘፈናቸውን፥ ድንፋታቸውንም ያደርጉ ነበር። 31እግዚአብሔርን እናመልከዋለን የሚሉ የእስራኤል ሕዝብ እንደዚሁ ያደርጉ ነበር። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ይጠብቁ ዘንድ፥ ጣዖትንም ከማምለክ ይርቁ ዘንድ፥ 32የሁዳዱን እህል ከመገባቸው፥ ወደ ምድሩም አዝመራ ካወጣቸው፥ ከማጓም ማሩን ከአጠገባቸው፥ መናውንም ከመገባቸው፥ ካባቶቻቸው ፈጣሪ በቀር ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩ ሙሴ በኦሪት የነገራቸውን ትእዛዙንና ሕጉን ግን አያደርጉም ነበር። 33የተመኙትንና የፈለጉትን አይነሳቸውም ነበር፤ እርሱም አምላካቸው ነውና የወደዱትን ይመግባቸው ነበር። 34እነርሱ ግን እግዚአብሔርን ማሳዘን አልተዉም፤ ደስ ባሰኛቸው ጊዜ እግዚአብሔርን ይዘነጉት ነበር። 35መቅሠፍትንም ባመጣባቸው ጊዜ ወደ እርሱ ይጮሁ ነበር፤ ካገኛቸውም መከራ ያድናቸው ነበር፤ ዳግመኛም በግልጥ ደስ ይላቸው ነበር፤ ብዙ ዘመንም ይኖሩ ነበር። 36ወዲያውም እንደ ቀድሞው እግዚአብሔርን ያሳዝኑት ዘንድ ፈጽመው ልባቸውን ይመልሱ ነበር፤ ያጠፏቸውም ዘንድ በዙሪያቸው ያሉ አሕዛብን ያስነሣባቸው ነበር፤ አስጨንቀውም ያስገብሩአቸው ነበር። 37ዳግመኛም ተመልሰው ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር ፈጥነው ይጮሁ ነበር። 38እርሱም ይቅር ይላቸው ነበር፤ በአማረ አኗኗራቸው ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔርን ስለ አገለገሉትና መሐላውን ስለ አጸናላቸው ስለ አባቶቻቸው ስለ ኖኅ፥ ስለ አብርሃምና ስለ ይስሐቅ፥ ስለ ያዕቆብም ነው እንጂ ስለ ራሳቸው አይደለም። 39እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደ ባሕር አሸዋ ዘራቸውን ያበዛ ዘንድ የወደዱትንና ትእዛዙን የጠበቁትን ወደዳቸው። 40እንደ ባሕር አሸዋ ያላቸው በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ከእስራኤል ልጆች ተለይተው ወደ ገሃነም የሚገቡ የኃጥኣን ነፍሳት ናቸው። 41በሰማይ ላይ እንደሚያበሩ ከዋክብት ናቸው የተባሉት ግን ከእስራኤል ልጆች ወገን የጻድቃን ነፍሳት ናቸው። እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ ብሎታልና፥ “ሌሊት ወደ ሰማይ እይ፤ መቍጠርም ትችል እንደ ሆነ የሰማይን ከዋክብት ቍጠራቸው፤ እንደዚሁም ልጆችህ ጻድቃን እንደ ሰማይ ከዋክብት በመንግሥተ ሰማይ ያበራሉ። 42“ዳግመኛም ወደ ባሕሩና ወደ ወንዙ ዳርቻ ተመልከት፤ በአሸዋው ውስጥ ያለውንም እይ፤ መቍጠርም ትችል እንደ ሆነ ቍጠር፤ በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ወደ ገሃነም የሚወርዱ ልጆችህ እንደዚሁ ናቸው፤” 43አብርሃምም በእግዚአብሔር አመነ፤ ስለዚህም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት፤ በምድርም ተስፋው ደረሰለት፤ ሚስቱ ሳራም ከአረጀች በኋላ ወንድ ልጅ ይስሐቅን አገኘች። 44ዳግመኛም ስለ እምነቱ በሰማያት መንግሥትን ያገኛል። ሙታን እንደሚነሡ፤ በጎ ሥራን የሠሩም ወደ ዘለዓለም ሕይወት፥ 45ክፉ የሠሩም በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ወደ ዘለዓለም ቅጣት እንደሚሔዱ አምኖአልና። በጎ ሥራ የሠሩ ጻድቃን ግን ከእርሱ ጋር ለዘለዓለም ይነግሣሉ። 46ክፉ የሠሩም ለዘለዓለም ይፈረድባቸዋል አሜን፥ አሜን።