1የሜዶን መንግሥት ትጠፋለች፤ የሮም መንግሥት ግን በመቄዶንያ መንግሥት ላይ ፈጽማ ትጸናለች፤ የነነዌም መንግሥት በፋርስ መንግሥት ላይ ትጸናለች። 2የኢትዮጵያ መንግሥትም በእስክንድርያ መንግሥት ላይ ትጸናለች፤ የሞዓብም መንግሥት በአማሌቅ ላይ ትጸናለች። 3ወንድም በወንድሙ ላይ ይነሣል፤ ይተላለቁም ዘንድ እንደ ተናገረ እግዚአብሔር በቀልን ያደርጋል። 4እንዲህም አለ፥ “መንግሥት በመንግሥት ላይ፥ ሕዝብም በሕዝብ ላይ፥ ሀገርም በሀገር ላይ ይነሣል። 5ክርክርም ይሆናል፤ ሰልፍ፥ ረኀብ ፥ ቸነፈር፥ ንውጥውጥታ፥ ድርቅም ይሆናል፤ ሰላምና ፍቅርም ይጠፋልና የእግዚአብሔር መቅሠፍት በእርሷ ላይ ይወርዳል። 6ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ መብረቅም የምታስፈራ የእግዚአብሔር ቀን በድንገት በደረሰች ጊዜ፥ 7የዚያን ጊዜ ሰው ሁሉ እንደ ሥራውና እንደ እጁ ድካም፥ እንደ ሥራውም ፍሬ ይቀበላል፤ እርሱ እግዚአብሔር እንዲህ ብሏልና፥ በፍርድ ቀንና እግራቸው በሚሰነካከልበት ቀን እበቀላቸዋለሁ፥ ለጥፋት የሚቈጠሩበት ቀን ደርሷልና። 8“የዚያን ጊዜ እግዚአብሔር በሕጉ የማይሄዱ ክፉ አድራጊዎችን በዘለዓለም ኵነኔ ያጠፋቸዋል፤ የይሁዳና የቆጵሮስ፥ የሰማርያና የደማስቆ፥ የባቢሎንም ሕዝብ፥ 9በምዕራብ ደሴትም የሚኖሩ ሕንደኬና ኖባ፥ ሳባና ግብፅም፥ ኢትዮጵያም በእነርሱም የሚኖሩ ሁሉ። 10ያንጊዜም ሰማይንና ምድርን የምገዛ፥ ክብርንና መወደድን የምሰጥ፥ የምገድልና የማድንም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 11ፀሐይን የማወጣ፤ ወደ መግቢያውም የምልከው እኔ ነኝ፤ ክፉውንና በጎውንም የማመጣ እኔ ነኝ። 12የደከማችሁበትን ገንዘብ፥ የላሞቻችሁንና የበጎቻችሁን መንጋም የሚበሉ የማታውቋቸውን አሕዛብ የማመጣ እኔ ነኝ። 13“ልጆቻችሁንም በፊታችሁ እየቀጠቀጡ ይማርኳቸዋል፤ እነርሱንም ማዳን አትችሉም። የእግዚአብሔርም መንፈስ ስላላደረባችሁ፥ የሰማችሁትንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልፈራችሁምና ወዛችሁንና ልምላሜያችሁን ይበላሉ። 14በአንተ ላይ የእግዚአብሔርን መንፈስ አያለሁና ብሎ ናቡከደነፆር ለነቢዩ ዳንኤል እንደ ነገረው የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ሰው ሁሉን ያውቃል። 15የእግዚአብሔርም መንፈስ ያደረበት ሰው ሁሉን ያውቃልና የተሰወረው ይገለጥለታል፤ የተገለጠውንና የተሰወረውንም ሁሉ ያውቃል እንጂ ከእግዚአብሔር መንፈስ የሚሰወር የለም። 16እኛ ግን ነገ የምንሞት ሰዎች ነንና ሰውረን የሠራነው ሥራ ሁሉ ይገለጣል። 17ወርቅንና ብርንም በእሳት እንደሚፈትኑት የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቁምና ኃጥኣን እንዲሁ በኋለኛዪቱ ቀን ይፈተናሉ። 18የዚያን ጊዜም የእስራኤል ልጆች ሁሉና የአሕዛብ ሁሉ ሥራዎቻቸው ይፈተናሉ።