1“ዳግመኛም ዳዊት፦ ሰዎች የመላእክትን እንጀራ በሉ ብሎ እንደ ተናገረ በምድረ በዳ መናን መገብኋቸው፤ በሚገባና በእውነት ያመልኩኝ ዘንድ ይኽን ሁሉ አደረግሁላቸው። 2እነርሱ ግን አላመለኩኝም፤ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። አሳዘኑኝ የእኔም ባልሆነ መንገድ ሔዱ። 3እኔም እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ። አምልኮቴን ቸል ብለዋልና፥ በምክሬና በሥርዐቴም አልጸኑምና እንደ እጃቸው ሥራ ቸል አልኋቸው፤ ወደ ገሃነም ቅጣትም አወርዳቸዋለሁ። 4ትእዛዜንም አልጠበቁምና፥ እኔም እቈጣቸዋለሁና በምድር ዘመናቸውን አሳንሳለሁ። 5ንጉሥ ሆይ! አንተም የምትሞትና የምትፈርስ፥ ነገ ትልና ብስባሽ ትቢያ የምትሆን ሰው አይደለህምን። 6ዛሬ ግን ለዘለዓለም እንደማይሞት ሰው ትመካለህ፤ ትኰራለህም። 7አንተስ ዛሬ ደኅና ሁነህ የምትታይ ነገ ግን የምትሞት ሰው ነህ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። 8ትእዛዜንና ቃሌን ብትጠብቅ ግን ማደሪያቸው ብሩህ ከሆነ፥ ዘውዶቻቸውም ከአማሩ፥ ዙፋኖቻቸውም የብርና የወርቅ ከሆኑ፥ በእነርሱም ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ያጌጡ ከሆኑና ፈቃዴን ከአደረጉ ከከበሩ ነገሥታት ጋራ ቅድስት ከተማን አወርስሃለሁ። 9በጎ ሥራን ለሚሠሩ ሰዎች የቀረበች ማደሪያ በምትሆን በከተማውም ውስጥ ደስ ይላችኋል። 10ክፋት ለሚሠሩ ሰዎች ግን ክቡራን ነገሥታት ወደሚገቡባት ወደዚያች ከተማ ይገቡ ዘንድ አይገባቸውም። 11ቃሌንና ሥርዐቴን አልጠበቁምና ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር።”