1“ነገሥታት ያለ እኔ ፈቃድ አይነግሡም፤ ጦም አዳሪዎችም ያለ ትእዛዜ አይደኸዩም፤ ኀይለኞችም ያለ ትእዛዜ አይበረቱም። 2እኔ ለዳዊት ባለሟልነትን ለሰሎሞንም ጥበብን ሰጠሁት፤ ለሕዝቅያስም ዘመኖችን ጨመርሁለት። 3የጎልያድንም ዘመን አሳነስሁ፤ ለሶምሶንም ኀይልን ሰጠሁት፤ ዳግመኛም ኀይሉን አደከምሁ። 4ባርያዬ ዳዊትንም ከረዓይታዊው ከጎልያድ እጅ አዳንሁት። 5“ዳግመኛም ከንጉሡ ከሳኦል እጅ፥ እንደዚሁም ከሚቃወመው ከሌላው ረዓይታዊ እጅ፥ ከሚቃወሙትና ከሚጠሉትም ሁሉ እጅ አዳንሁት፤ ትእዛዜን ጠብቋልና። 6እኔም እርሱን ወደድሁ፤ ትእዛዜን የሚጠብቁ ነገሥታትንና መኳንንትንም እወዳድቸዋለሁ፤ እነርሱም ደስ አሰኝተውኛልና በጠላቶቻቸው ላይ ኀይልንና ድልን እሰጣቸዋለሁ። 7ዳግመኛም የአባቶቻቸውን ምድር ይወርሱ ዘንድ ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን የነጻችና የበራች ምድረ ርስትን እሰጣቸዋለሁ።