1“ቃሌን ስለ ተላለፈ አሳዝኖኛልና የሳኦልን ወገን ጠላሁ። 2እኔም ቸል አልሁት፤ ዳግመኛም ቃሌን አልጠበቀምና ከወገኑ አላነግሥም። 3እንደዚሁም ቃሌን ከማይጠብቁ፥ በሕጌና በሥርዐቴ ከማይሔዱ መንግሥቴንና ስጦታዬን እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ከልጆቻቸው እከለክላለሁ። 4ባገነንኋቸው ጊዜ አያገኑኝምና፥ በአከበርኳቸውም ጊዜ አያከብሩኝምና አጠፋቸዋለሁ እንጂ ደግሜ ላከብራቸው አልመለስም። 5በጎ ነገርን ባደረግሁላቸውም ጊዜ አያደርጉልኝም፤ ይቅር ባልኋቸውም ጊዜ ይቅር አይሉልኝም። 6በሁሉም ላይ ገዢ ባደረግኋቸው ጊዜ ገዢ አላደረጉኝም፤ ከሁሉ ይልቅ ባከበርኋቸውም ጊዜ አያከብሩኝም፤ ትእዛዜንም አይጠብቁም። 7“እኔም የሰጠኋቸውን ስጦታ ነሳኋቸው፤ በቍጣዬም እንደ ማልሁ አልመልስላቸውም፤ ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያከበረኝን አከብረዋለሁ፤ የወደደኝንም እወድደዋለሁ። 8ያላከበሩኝን፥ ሕጌንም ያልጠበቁትን ከሰጠኋቸው ስጦታ እለያቸዋለሁ። 9ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የወደደኝን እወድደዋለሁ፤ ያገነነኝንም አገንነዋለሁ፤ 10እኔ እግዚአብሔር ሁሉን የምችል ነኝና በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር ከእጄ የሚያመልጥ የለም፤ የምገድል፥ የማድንም፥ የምገርፍ፥ ይቅርም የምል እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 11ክብርና ገናናነትም የእኔ ነው፤ የወደድሁትን አከብረዋለሁ፤ የጠላሁትንም አዋርደዋለሁ፤ የምፈርድና የምበቀል እኔ ነኝና። 12“የሚወድዱኝንና ስሜን ሁልጊዜ የሚጠሩትን ይቅር የምል እኔ ነኝ፤ ለባለጠጋውና ለድሃው ምግብ የምመግብ እኔ ነኝ። 13ሰውን ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ወፎችንና እንስሶችን፥ በባሕር ያሉ ዓሣዎችንና አውሬዎችን፥ እባቦችንም እመግባለሁ። 14አዞዎችንና ዓሣ አንበሪዎችን፥ ሽኮኮዎችንና ጉማሬዎችን፥ አቈስጣንም እመግባለሁ። 15በውኃ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ በአየር ላይ የሚበርረውም ሁሉ የኔ ነው። 16በሚገባና በሚያስፈልግ ሁሉ እኔን ለሚፈልጉኝ ሁሉ የምመግብ እኔ ነኝ።