1የግብፅም ሰዎች የእስራኤልን ልጆች በጭንቅ፥ ጡብ በማሠራት፥ በሚያሠሩአቸውም ሥራ ሁሉ፥ ያለ ገለባ ጭቃ በማስረገጥ በአስጨነቋቸው ጊዜ፥ 2ሠሪዎችን የሚያፋጥኑ አለቆችንም በእነርሱ ላይ ሾመው ባሠሯቸው ጊዜ የግብፅን ጡብ ሁሉ ከመሥራት ያድናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮሁ። 3የዚያን ጊዜም የሚረዷቸውን ሙሴንና አሮንን ላከላቸው፤ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን አገዛዝ ቤት ወገኖቹን ያወጡ ዘንድ እግዚአብሔር ልኳቸዋልና ከጡብ ሥራ አዳኗቸው፤ ለእግዚአብሔር እንዳይገዙ፥ በምድረ በዳም መሥዋዕት እንዳይሠዉ በትዕቢቱ እስራኤልን ማሰናበት እንቢ ብሏልና። 4እግዚአብሔርም ትዕቢተኞችን ቸል ይላቸዋልና ፈርዖንን ስለ ትዕቢቱ ከሠራዊቱ ጋር በኤርትራ ባሕር አሰጠመው። 5እንዲሁም ነገሥታትና መኳንንት ሲሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል የሚሉ፥ ፈቃዱንም ይፈጽሙለት ዘንድ፥ በበጎም ነገር ለሚያገለግሉ ሰዎች ደመወዛቸውን ይሰጧቸው ዘንድ፥ ገናና ስሙንም ያከብሩ ዘንድ በሾማቸውና በአነገሣቸው ሁሉ መልካም ያልሠሩትን ቸል ይላቸዋል። 6“መንግሥቴን ቢያቀኑ መንግሥታቸውን አቀናላቸዋለሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። 7መልካም አድርጉልኝ፤ እኔም መልካም አደርግላችኋለሁ፤ ትእዛዜን ጠብቁ፤ እኔም ሰውነታችሁን እጠብቃለሁ፤ በትእዛዜ ሒዱ፤ እኔም እንደ ልቡናችሁ እሔዳለሁ። 8እኔን ውደዱ፤ እኔም ሕይወታችሁን እወድዳለሁ፤ ወደ እኔ ተጠጉ፥ እኔም አጸናችኋለሁ። 9በእኔ እመኑ፤ እኔም አድናችኋለሁ ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። 10እናንተ አግድም አግድም አትሒዱ፤ እናንተ ቅረቡኝ፤ እኔም እቀርባችኋለሁ፤ ቀና መንገዶችን እወድዳለሁና ይላል ሁሉን የሚችል እግዚአብሔር። ኃጥኣንና ከዳተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ የልቡናችሁንም ክፋት አስወግዱ፤ 11እኔም ቍጣዬን ከእናንተ አርቃለሁ፤ በይቅርታና በምሕረትም እመለስላችኋለሁ። 12በደልን የሚሠሩ ወንጀለኞች ጠላቶችንም ከእናንተ አርቃለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትን ከተገናኙት ከጠላቶቹ ከብዙ ተንኰላቸው፥ አርበኛ ከሆነ ከጎልያድም እጅ፥ ይገድለውም ዘንድ ከፈለገው ከሳኦል እጅ፥ መንግሥቱን ይወስድ ዘንድ ከወደደ ከልጁ ከአቤሴሎምም እጅ እንዳዳንሁት፥ 13ሕጌን የሚጠብቁ፥ ፈቃዴንም የሚፈጽሙ ሰዎችንም እንደ እርሱ አድናቸዋለሁ፤ ክብርንም አወርሳቸዋለሁ፤ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም ደስ ይላቸው ዘንድ በሁሉ ላይ አነግሣቸዋለሁ።” 14እርሱ ሕጻን ሆኖ ሳለ ከሕጻንነቱ ጀምሮ በአማረ አኗኗሩ እግዚአብሔር እንደ መረጠው እንደ ሳሙኤል በአማረ አኗኗራቸው እግዚአብሔርን ካገለገሉ ቡሩካን ነገሥታት ጋር አንድ ይሆናሉ። 15ሥራው መልካም ለሆነ ለአረጋዊው ካህን ለኤሊ ይነግረው ዘንድ በእግዚአብሔር አምላክ ማደሪያ ሲያገለግል ለነቢዩ ሳሙኤል ነገረው። 16በእግዚአብሔርም ቤት እያገለገለ በአደገ ጊዜ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሕዝቡን እንዲሾምና ነገሥታቱን እንዲቀባ አደረገው። እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች የመረጠውን ወገን ይሾም ዘንድ ወድዶታልና የፈጠረው የእግዚአብሔርን ፈቃድ በፈጸመ ጊዜ በእጁ ቅብዐ መንግሥትን ሰጠው። 17ሳኦልም በመንግሥቱ ሳለ እግዚአብሔር ነቢዩ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፥ “ከይሁዳ ወገን የተወለደ የዕሤይ ልጅ ዳዊትን ወድጄዋለሁና ሒድና ቅባው።”