1ከዚህም በኋላ ልጆቹ በዙ፤ ከእነርሱም እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑትና የሚያከብሩት፥ ትእዛዙንም የማያፈርሱ ነበሩ። 2የሆነውንና የሚሆነውን የሚናገሩ ነቢያትም ነበሩ፤ ከልጆቹም ሐሰት የሚናገሩ፥ ሰውንም የሚበድሉ ኀጢአተኞች ነበሩ፤ የአዳም የበኸር ልጁ ቃየል ክፉ ሆነ፤ ወንድሙ አቤልንም ገደለው። 3ወንድሙን አቤልንም ስለ ገደለ እግዚአብሔር በቃየል እጅግ ተቈጣ፤ ደሙንም ስለ ጠጣች እግዚአብሔር ምድርን ተቈጣት። 4እግዚአብሔርም ቃየልን፥ “ወንድምህ አቤል ወዴት አለ?” አለው ቃየልም በልቡ ትዕቢት “የወንድሜ የአቤል ጠባቂ እኔ ነኝ?” አለ። 5አቤልም ጻድቅ ነበረ፤ ቃየል ግን ደጉን ሰው ወንድሙን አቤልን በመግደል ኃጥእ ሆነ። 6ዳግመኛም ጻድቅ ሴት ተወለደ፤ አዳም ሠላሳ ሴቶችንና ሠላሳ ወንዶችን ወልዷልና። ከእነርሱም ደጋጎች ነበሩ፤ ክፉዎችም ነበሩ። 7ከእነርሱም ነቢያትና ጻድቃን ነበሩ፥ ከእነርሱም ኃጥኣንና ሸንጋዮች ነበሩ። 8ከእነርሱም የአባታቸውን የአዳምን ፈቃድ፥ ከአዳም ጀምሮ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እስከ ጠበቀ እስከ ጻድቁ ኖኅ ድረስ፥ ለልጁ ለሴት የነገረውንም ሁሉ የሚፈጽሙ ደጋጎችና ቡሩካን ነበሩ። 9እርሱም ለልጆቹ የእግዚአብሔርን ሕግ አስጠበቃቸው፤ የእግዚአብሔርንም ሕግ እንዳያፈርሱ አባታቸው ኖኅ እንደ ነገራቸው እነርሱም ለልጆቻቸው ይነግሩ ዘንድ፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ ይጠብቁ ዘንድ አደራ አላቸው። 10እነርሱም ከእነርሱ በኋላ ለልጆቻቸው እያስተማሯቸው ኖሩ። 11ሰይጣን ግን አባቶቻቸውን ለመቃብር በአደረሱ፥ ሥዕል ባለባቸው ጣዖታት አድሮ፥ እሺ የሚሉትን ሰዎች ሲወጋቸውና ሲናገራቸው ኖረ፤ ያም የክፋት መምህር ያዘዛቸውን ሁሉ ሲያደርጉ ኖሩ። 12የእግዚአብሔርንም ፈቃድ የሚፈጽም ጻድቅ አብርሃም እስኪነሣ ድረስ እንደ ሥርዐታቸው ጣዖቱን ሲያመልኩ ኖሩ። 13እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋራ በእሳትና በአውሎ ቃል ኪዳን አደረገ። ከዘመዶቹ ተለይቶ በጽድቅ መንገድ መሔድን እርሱ ቀድሞአልና። 14እግዚአብሔርም ለእርሱና ለልጆቹ ምድረ ርስትን እስከ ዘለዓለም ድረስ ይሰጣቸው ዘንድ ማለለት። 15እንዲሁም ለይስሐቅ የአባቱን የአብርሃምን ርስት ይሰጠው ዘንድ ማለለት፤ ለያዕቆብም እንዲሁ የአባቱን የይስሐቅን ርስት ይሰጠው ዘንድ ማለለት፤ 16ከእነርሱም በኋላ ዘራቸውን የያዕቆብን ልጆች ከዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ነገሥታትና ካህናት አደረጋቸው፤ ባረካቸው፤ “ብዙ፥ የብዙ ብዙም ሁኑ” አላቸው። 17የአባቶቻቸውንም ርስት ሰጣቸው፤ ነገር ግን እየመገባቸው፥ በሁሉም እየወዳደቸው ሳለ እግዚአብሔርን ማሳዘን አልተዉም። 18ባጠፋቸውም ጊዜ ያንጊዜ ይፈልጉታል፤ ተመልሰውም ወደ እግዚአብሔር ይገሠግሣሉ፤ እግዚአብሔርም ይወድዳቸዋልና ይቅር ይላቸዋል። 19ስለ ራሳቸውም አይደለም፤ ስለ አባቶቻቸው ነው እንጂ፥ ለፈጠረው ሁሉ መሓሪና ይቅር ባይ ነውና። 20የተራበች ሰውነትንም ያጠግብ ዘንድ ቀኝ እጁን በበረከት ይዘረጋል፤ ለምግብ እህልን ያበዛ ዘንድ ለምሕረት ዐይኑን ይገልጣል። 21ለቍራዎች ጫጩቶችና ለሚጠሩት ሁሉ ምግብን ይሰጣቸዋል፤ ወደ እርሱም በጮሁ ጊዜ፥ የእስራኤልን ልጆች ከጠላቶቻቸው እጅ ያድናቸዋል። 22ዳግመኛም ያሳዝኑት ዘንድ ይመለሳሉ፤ እርሱም በዙሪያቸው ያሉ ጠላቶቻቸውን አሕዛብን ልኮ ያጠፏቸዋል፥ ይገድሏቸዋል፥ ይማርኳቸዋልም። 23ዳግመኛም በጩኸትና በልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤ እርሱም ረዳትን ይልክላቸዋል፤ በነቢያት እጅም ያዳነበት ጊዜ አለ። 24በመሳፍንትም እጅ ያዳነበት ጊዜ አለ፤ እግዚአብሔርንም ባሳዘኑት ጊዜ ጠላቶቻቸው አስገበሯቸው፤ ማረኳቸውም። 25ዳዊትም ተነሥቶ ከኢሎፍላውያን እጅ አዳናቸው፤ ዳግመኛም እግዚአብሔርን አሳዘኑት፤ የሚያስጨንቋቸውንም አስነሣባቸው። 26በዮፍታሔም እጅ ያዳነበት ጊዜ አለ፤ ዳግመኛም ያዳናቸውን እግዚአብሔርን ዘነጉት። እግዚአብሔር ፍዳውን አምጥቶባቸዋልና ክፉ የሆኑ፥ መከራን የሚያጸኑባቸውን፥ ፈጽመውም የሚማርኳቸውን ጠላቶችን ይልክባቸዋል። 27ዳግመኛም በተጨነቁ ጊዜ ወደ እርሱ ጮሁ፤ እርሱም በጌዴዎን እጅ አዳናቸው፤ ዳግመኛም በእጃቸው ሥራ እግዚአብሔርን አሳዘኑት። 28እርሱም ዳግመኛ የሚያሰቃዩአቸውን ላከባቸው፤ ተመልሰውም ወደ እግዚአብሔር አለቀሱ፤ ጮኹም። 29ዳግመኛም በሶምሶን እጅ አዳናቸው፤ ጥቂትም ዐረፉ። አስቀድመውም በሠሩት ክፋታቸው እግዚአብሔርን ያሳዝኑት ዘንድ ተነሡ። 30እርሱም ዳግመኛ የሚያስጨንቋቸውን ሌሎችን ላከባቸው። ዳግመኛም ረዳትን ይልክላቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፤ አለቀሱም፤ በባርቅና በዲቦራም እጅ አዳናቸው። 31ዳግመኛም እግዝአብሔርን እያመለኩት ጥቂት ዘመን ኖሩ፤ ዳግመኛም ረሱት፤ በቀደመ ክፋታቸውም እግዚአብሔርን አሳዝኑት። 32እርሱም የሚያስጨንቋቸውን ሌሎችን ላከባቸው፤ ዳግመኛም በዮዲት እጅ አዳናቸው፤ ዳግመኛም ጥቂት ወራት ተቀምጠው እንደ ቀደመው እግዚአብሔርን በክፋታቸው ያሳዝኑት ዘንድ ተነሡ። 33እርሱም የሚገዟቸው አሕዛብን አስነሣባቸው፤ እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፤ አለቀሱም፤ በማታትዩና በልጆቹ እጅ በቤት ማዕዘን ላይ አዳናቸው። 34የይሁዳን ሀገር ይወጋ ዘንድ የመጣው አሂሜሌክ የረዓይታዊውን ራስ መትቶታልና፤ ያም ራዓይታዊ በሞተ ጊዜ ሠራዊቱ ተበተኑ፤ ሸሹም፤ የእስራኤልም ልጆች እስከ ኢያቦቅ ወጉአቸው፤ ከእነርሱም አንድ እንኳ የሚሸሽ አላስቀሩም። 35ከዚህ በኋላ ጥቂት ቈይተው እግዚአብሔርን ያሳዝኑት ዘንድ ተነሡ፤ እርሱም የሚገዟቸው አሕዛብን አስነሣባቸው፤ ዳግመኛም ወደ እግዚአብሔር ጮሁ፤ አለቀሱም፤ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ አሳዝነውታልና፥ ሕጉንም ረስተዋልና እግዚአብሔር ጩኸታቸውንና ልቅሷቸውን ቸል አለ። 36ማርከውም ከካህናቶቻቸው ጋር ወደ ከለዳውያን ሀገር ወሰዷቸው። 37በዚያም ኀጢአትን እየሠሩ፥ ጣዖትንም እያመለኩ ከዳተኞች የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን ማሳዘንን አልተዉም። ከማረኩዋቸው ከአሕዛብም ጋር ተቀላቀሉ። 38እግዚአብሔርም በዚያ በኀጢአታቸው አንድ ጊዜ ያጠፋቸው ዘንድ ተቈጣ፤ በንጉሡም ሣጥን እልፍ ወርቅን አግብቶ በታወቀች ቀን ያጠፋቸው ዘንድ በነገረው ጊዜ ከሕንደኬ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በፋርስ ሀገር ልጆቻቸውን እንዳያስቀር በንጉሡ በአርጤክስስ ልቡና ቍጣን አሳደረ። 39እንዲህም አደረገ፥ በንጉሡ ፈቃድ የመልእክት ደብዳቤ ጻፈ፤ ወደ ፋርስም ሀገር ያደርስ ዘንድ በእጁ ያለ ማኅተምን ሰጠው። 40ንጉሥ እንዳዘዘ ሊያጠፋቸው በወደደባት ባንዲት ቀን ያጠፋቸው ዘንድ ማኅተምን ሰጠው፤ ብዝበዛቸውን ወርቁንና ብሩን ግን ወደ ንጉሡ ሣጥን ያገቡ ዘንድ አዘዘ። 41ያንጊዜም የእስራኤል ልጆች ይህን በሰሙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ፈጽመው ጮሁ፤ አለቀሱም፤ ለመርዶክዮስም ነገሩት፤ መርዶክዮስም ለአስቴር ነገራት። 42አስቴርም“ጹሙ፤ ጸልዩም፤ የእስራኤል ልጆች ወገኖችም ሁሉ ባላችሁበት ቦታ ወደ እግዚአብሔር ጩሁ” አለች። 43መርዶክዮስም ማቅ ለበሰ፤ በራሱም ትቢያን ነሰነሰ፤ የእስራኤልም ልጆች ባሉበት ሀገር ጾሙ፤ ጸለዩም፤ ንስሓም ገቡ። 44አስቴርም እጅግ አለቀሰች፤ ንግሥትም ስትሆን ማቅ ለበሰች፤ ትቢያንም ነሰነሰች፤ ራሷንም ተላጨች፤ የፋርስም ንግሥታት እንደሚያደርጉት ሽቱን አልተቀባችም፤ በጥልቅ ልቡናዋም ወደ አባቶችዋ ፈጣሪ ወደ እግዚአብሔር ጮኸች፤ አለቀሰችም። 45ስለዚህም በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ፊት ሞገሰን ሰጣት፤ ስለ አባቶችዋም ፈጣሪ ታላቅ ግብዣን አደረገች። 46ንጉሡና ሐማም አስቴር ወደ አዘጋጀችው ምሳ ገቡ፤ በዚያም በመርዶክዮስ ላይ ያደርግ ዘንድ እንደ ወደደ እግዚአብሔር ለሐማ ፍዳውን ከፈለው፤ በረጅም እንጨት ላይም ሰቀሉት። 47በፈቃዳቸው ሁሉ እንዳሉ እስራኤልን ይተዋቸው ዘንድ፥ እንዳያስገብሯቸውም፥ እንዳይቀሟቸውም፥ እንዳይበድሏቸውም፥ ገንዘባቸውንም እንዳይወስዱባቸው የንጉሡ ደብዳቤ ተላለፈ። 48ሀገራቸውን እንዳያጠፉ፥ ከብቶቻቸውንም እንዳይማርኩ፥ ነገር ግን በፋርስ ሀገር ሁሉ ይወድዷቸውና ያከብሯቸው ዘንድ ደብዳቤው ተላለፈ። በንስሓ ወደ እርሱ በለመኑና በጮኹ ጊዜ እግዚአብሔር እስራኤልን እንዲህ ይቅር ይላቸዋልና። 49ባሳዘኑትም ጊዜ የሚያስጨንቋቸው አሕዛብን ያስነሣባቸዋል፤ ያንጊዜም ረዳታቸውን ይልክላቸው ዘንድ መከራ ከሚያጸኑባቸው ከአሕዛብም እጅ ያድናቸው ዘንድ ፈጽመው ያለቅሳሉ፤ ይጮኻሉም።