1ዓለሙን ሁሉ ከአለመኖር ፈጠረ፤ ተራሮችንና ኮረብቶችንም ፈጽሞ አዘጋጀ፥ ምድርንም በውኃ ላይ አጸናት፤ እንዳትነዋወጥም በአሸዋ ወሰናት፤ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ቃሉ “ብርሃን ይሁን” ብሏልና። 2ዓለም በጨለማ ሳለ ብርሃን ሆነ፤ እግዚአብሔርም ሥራውን ሠራ፤ በሚገባና በተስተካከለ ዓለምን አዘጋጅቶ አጸናት፤ ምሽትና ጨለማ ይሁን አለ፤ ምሽትና ጨለማም ሆነ። 3ዳግመኛም እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን አለ፤ ነጋ፤ ብርሃንም ሆነ፤ የላይኛውንም ውኃ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አደረገው። 4እንደ ድንኳንም ዘረጋው፤ በነፋስም አጸናው፤ የታችኛውንም ውኃ በባሕሩ ጥልቅ በታች አኖረው። 5የባሕሩንም ቍልፍ በአሸዋ ዘጋው፤ ወደ ታችም እንዳይሰጥሙ በመንፈሱ አጸናቸው፤ አራዊትንና እንስሳትንም በውስጧ አኖራቸው፤ ታላላቆች እንስሳትንም፤ ቍጥር የሌላቸው የሚታዩና የማይታዩትንም በውስጧ አኖራቸው። 6በሦስተኛው ቀን እግዚአብሔር በምድር ላይ አትክልትን፥ ሣሩን ሁሉ፥ እንጨቶችን፥ በየወገናቸው የሚያፈሩ ፍሬዎችንም፥ 7ሊያዩትም ያማረ፥ ሊበሉትም የጣፈጠ ፈጠረ፤ የሕይወት ዛፍን፥ ሣርንም፥ ዘሩ ከውስጡ የሚገኝ ተክልንም ሁሉ ፈጠረ። ለከብቶችና ለአውሬዎች፥ ለወፎችም መብልን ፈጠረ፤ ለፈጠረውም ሁሉ ምግብን ሰጠ። 8ማታም ሆነ፤ ነጋም፤ በአራተኛዪቱም ቀን እግዚአብሔር በሰማይ ጠፈር ብርሃን ይሁን አለ፤ እግዚአብሔርም ፀሐይን፥ ጨረቃንና ከዋክብትን ፈጠረ። በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ፥ መዓልትና ሌሊትንም ይመግቧቸው ዘንድ በሰማይ ጠፈር ሾማቸው። 9ከዚህም በኋላ ፀሐይ፥ ጨረቃና ከዋክብት፥ መዓልትና ሌሊትም ተፈራረቁ። 10በአምስተኛዪቱም ቀን እግዚአብሔር በውኃ ውስጥ የሚኖሩ አራዊትንና እንስሳትን ሁሉ ፈጠረ፤ በሰማይ ላይ የሚበሩ ወፎችንም ሁሉ፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ ይህንም ሁሉ እግዚአብሔር ፈጠረ። 11በስድስተኛዪቱም ቀን አውሬዎችንና እንስሳትን፥ ትሎችንም ፈጠረ፤ ሁሉንም ፈጥሮና አዘጋጅቶ አዳምን በአርአያውና በምሳሌው ፈጠረው። 12የፈጠራቸውን እንስሳትና አውሬዎችን ሁሉ ይነግሥባቸው ዘንድ ሰጠው፤ ዳግመኛም እንስሳትንና አራዊትን ሁሉ፥ ዓሣዎችንም ሁሉ፥ በባሕር ያሉ ዓሣ አንበሪዎችንም ሁሉ ሰጠው። 13በምድር ላይ ያሉ ላሞችን ሁሉና በጎችንም፥ የሚታየውንና የማይታየውን እንስሳ ሁሉ ሰጠው። 14በመልኩና በምሳሌው የፈጠረው አዳምንም በገነት አኖረው፤ ይበላ ዘንድ፥ ገነትንም ይኰተኵታት ዘንድ፥ በዚያ እግዚአብሔርን ያመሰግነው ዘንድ አዘዘው። 15የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ እንዳያፈርስ ሞትን ከሚያመጣ፥ ክፉና በጎንም ከሚያሳውቅ ዛፍ እንዳይበላ አዘዘው። 16“ከዚያ ዛፍ በበላችሁ ጊዜ ሞትን ትሞታላችሁ” ብሏልና። 17እናታችን ሔዋን በእባብ ማሳት ተሸንግላ ከዚያ ከዕፀ በለስ በላች፤ ለአባታችን ለአዳምም ሰጠችው። 18ከዚያም ዛፍ በላ፤ በራሱና በልጆቹም ላይ ሞትን አመጣ። 19ትእዛዙን አፍርሷልና፥ እግዚአብሔር ከእርሱ አትብላ ብሎ ካዘዘው ከዚያም ከዕፀ በለስ በልትዋልና እግዚአብሔር በአባታችን በአዳም ላይ ተቈጣ፤ ከገነትም አስወጥቶ ሰደደው፤ ያርሳት ዘንድ፥ በፊቱም ወዝ የድካሙን ዋጋ ይበላ ዘንድ ትእዛዙን በአፈረሰ ጊዜ ስለ እርሱ የረገማትን፥ አሜከላና እሾህን የምታበቅል ያችን ምድር ሰጠው። 20እግዚአብሔርም ወደዚች ምድር በአወጣው ጊዜ አዳም ወደ ኀዘንና ወደ ልብ ትካዜ ተመለሰ። ምድርንም ያርሳት ዘንድ፥ በፊቱ ወዝ፥ በልፋትና በድካምም ይበላ ጀመር።