ሃሌ ሉያ።
1ሃሌ ሉያ የእግዚአብሔርን ስም አመስግኑ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ አመስግኑት 2በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ 3እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ ለስሙ ዘምሩ መልካም ነውና 4እግዚአብሔር ያዕቆብን ለራሱ እስራኤልንም ለመዝገቡ መርጦታልና 5እግዚአብሔር ታላቅ እንደ ኾነ ጌታችንም ከአማልክት ዅሉ እንዲበልጥ ዐውቄያለኹና 6በሰማይና በምድር በባሕርና በጥልቆች ዅሉ እግዚአብሔር የወደደውን ዅሉ አደረገ 7ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል በዝናብ ጊዜ መብረቅን አደረገ ነፋሳትንም ከመዛግብቱ ያወጣል 8የግብጽን በኵር ልጆች ከሰው ዠምሮ እስከ እንስሳ ድረስ መታ 9ግብጽ ሆይ በመካከልሽ በፈርዖንና በባሪያዎቹ ዅሉ ላይ ተኣምራትንና ድንቅን ሰደደ 10ብዙ አሕዛብን መታ ብርቱዎችንም ነገሥታት ገደለ 11የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን የባሳንንም ንጉሥ ዐግን የከነዓንን መንግሥታት ዅሉ ገደለ 12ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ለእስራኤል ለሕዝቡ ርስት ሰጠ 13አቤቱ ስምኽ ለዘለዓለም ነው ዝክርኽም ለልጅ ልጅ ነው 14እግዚአብሔር ለሕዝቡ ይፈርዳልና ባሪያዎቹንም ይረዳልና 15የአሕዛብ ጣዖታት የብርና የወርቅ የሰው እጅ ሥራ ናቸው 16አፍ አላቸው አይናገሩምም ዐይን አላቸው አያዩምም 17ዦሮ አላቸው አይሰሙምም እስትንፋስም በአፋቸው የለም 18የሚሠሯቸው ዅሉ የሚታመኑባቸውም ዅሉ እንደ እነርሱ ይኹን 19የእስራኤል ቤት ሆይ እግዚአብሔርን ባርኩት የአሮን ቤት ሆይ እግዚአብሔርን ባርኩት 20የሌዊ ቤት ሆይ እግዚአብሔርን ባርኩት እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ እግዚአብሔርን ባርኩት 21በኢየሩሳሌም የሚያድር እግዚአብሔር ከጽዮን የተባረከ ነው ሃሌ ሉያ