1በንጉሡ በአርተሰስታ በሃያኛው ዓመተ መንግሥት በኔሳን ወር የወይን ጠጅ በፊቱ ነበር፤ ጠጁንም አንሥቼ ለንጉሡ ሰጠሁት። በፊቱም ሌላ ሰው አልነበረም። 2ንጉሡም፥ “ሳትታመም ፊትህ ለምን አዘነ? ይህ የልብ ኀዘን ነው እንጂ ሌላ አይደለም” አለኝ። እጅግም ብዙ አድርጌ ፈራሁ። 3ንጉሡንም፥ “ንጉሡ ለዘለዓለም ይኑር፤ የአባቶች መቃብር ያለባት ከተማ ተፈትታለችና፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋልና ፊቴ ስለ ምን አያዝን?” አልሁት። 4ንጉሡም፥ “ምን ትለምነኛለህ?” አለኝ። እኔም ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይሁ። 5ንጉሡንም፥ “ንጉሡን ደስ ቢያሰኝህ፥ ባሪያህም በፊትህ ሞገስ ቢያገኝ፥ እሠራው ዘንድ ወደ ይሁዳ ወደ አባቶች መቃብር ከተማ ስደደኝ” አልሁት። 6ንግሥቲቱም፦ በአጠገቡ ተቀምጣ ሳለች ንጉሡ፥ “መንገድህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል? መቼስ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ይሰድደኝ ዘንድ ደስ አለው፤ እኔም ጊዜውን ነገርሁት፤ እርሱም አሰናበተኝ። 7ንጉሡንም፥ “ንጉሥ ደስ ቢለው፥ እስከ ይሁዳ ሀገር እንዲያደርሱኝ በወንዝ ማዶ ላሉት ገዦች ደብዳቤ ይስጠኝ፤ 8በቤቱም አጠገብ ላለው ለግንብ በሮች፥ ለከተማውም ቅጥር፥ ለምገባበትም ቤት እንጨት እንዲሰጠኝ ለንጉሡ ዱር ጠባቂ ለአሳፍ ደብዳቤ ይሰጠኝ” አልሁት። ንጉሡም ሁሉን ሰጠኝ። የከበረች የአምላኬ እጅ ከእኔ ጋር ነበረችና። 9በወንዙም ማዶ ወዳሉት ሀገረ ገዦች መጥቼ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው። ንጉሡም ከእኔ ጋር የሠራዊቱን አለቆችና ፈረሰኞች ልኮ ነበር። 10ሖሮናዊውም ሰንባላጥና አገልጋዩ አሞናዊው ጦብያ ለእስራኤል ልጆች መልካምን ነገር የሚሻ ሰው እንደ መጣ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተበሳጩ። 11ወደ ኢየሩሳሌምም ደረስሁ፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥሁ። 12በሌሊትም ተነሣሁ፤ ከእኔም ጋር ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርም ለኢየሩሳሌም አደርገው ዘንድ በልቤ ያኖረውን ለማንም አላስታወቅሁም፤ ተቀምጬበት ከነበረው እንስሳ በቀር ከእኔ ጋር ምንም እንስሳ አልነበረም። 13በሸለቆውም በር ወጣሁ፤ ወደ በለስም ምንጭና ወደ ጕድፍ መጣያው በር ሄድሁ፤ የፈረሰውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር፥ በእሳትም የተቃጠሉትን በሮችዋን ተመለከትሁ። 14ወደ ምንጩም በርና ወደ ንጉሡም መዋኛ አለፍሁ፤ ተቀምጬበት የነበረው እንስሳም የሚያልፍበት ስፍራ አልነበረም። 15በሌሊትም በፈፋው በኩል ወጥቼ ቅጥሩን ተመለከትሁ፤ በሸለቆውም በር ገባሁ፤ እንዲሁም ተመለስሁ። 16ጠባቆች ግን ወዴት እንደ ሄድሁ፥ ምን እንዳደረግሁም አላወቁም ነበር፤ ለአይሁድና ለካህናቱ፥ ለታላላቆችና ለሹሞቹም፥ ሥራም ይሠሩ ለነበሩት ለሌሎች እስከዚያ ጊዜ ገና አልተናገርሁም ነበር። 17እኔም፥ “እኛ ያለንበትን ጕስቍልና፥ ኢየሩሳሌም እንደ ፈረሰች፥ በሮችዋም በእሳት እንደ ተቃጠሉ ታያላችሁ። አሁንም ከእንግዲህ ወዲህ መሳለቂያ እንዳንሆን ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንሥራ” አልኋቸው። 18የአምላኬም እጅ በእኔ ላይ መልካም እንደ ሆነች፥ ንጉሡም የነገረኝን ቃል ነገርኋቸው። “ተነሡ እንሥራ” አልኋቸው። እጆቻቸውንም ለበጎ ሥራ አበረቱ። 19ሖሮናዊውም ሰንባላጥ፥ አገልጋዩም አሞናዊው ጦቢያ፥ ዓረባዊውም ጌሳም በሰሙ ጊዜ በንቀት ሳቁብን፤ ቀላል አድርገውንም ወደ እኛ መጡና፥ “ይህ የምታደርጉት ነገር ምንድን ነው? በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን?” አሉ። 20እኔም መልሼ፥ “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፤ እኛም ንጹሓን ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ዕድል ፋንታና መብት፥ መታሰቢያም የላችሁም” አልኋቸው።