1የኬልቅያ ልጅ የነህምያ ቃል። 2ከወንድሞች አንዱ ሐናኒ፥ ከእርሱም ጋር ሌሎች ሰዎች ከይሁዳ መጡ፤ እኔም የዳኑትን፥ ከምርኮም የተረፉትን የአይሁድን ነገር፥ የኢየሩሳሌምንም ነገር ጠየቅኋቸው። 3እነርሱም፥ “በዚያ ስፍራ ያሉት ከምርኮ የተረፉት ቅሬታዎች በታላቅ መከራና ስድብ አሉ፤ የኢየሩሳሌምም ቅጥር ፈርሶአል፥ በሮችዋም በእሳት ተቃጥለዋል” አሉኝ። 4ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ፤ አያሌ ቀንም አዝን ነበር፤ በሰማይም አምላክ ፊት እጾምና እጸልይ ነበር፤ እንዲህም አልሁ፦ 5“አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ለሚወድዱህና ትእዛዝህን ለሚያደርጉ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ታላቅና የተፈራህ አምላክ ሆይ፥ 6እኔ ባሪያህ ዛሬ በፊትህ ስለ ባሪያዎችህ ስለ እስራኤል ልጆች ሌሊትና ቀን የምጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ጆሮዎችህ ያድምጡ፤ ዐይኖችህም ይከፈቱ፤ በአንተ ላይም ያደረግነውን የእስራኤልን ልጆች ኀጢአት ለአንተ እንናዘዛለን፤ እኔም፥ የአባቴም ቤት በድለናል። 7እኛም በአንተ ላይ እጅግ ክፉ ሠርተናል፤ ለባሪያህም ለሙሴ ያዘዝኸውን ትእዛዝና ሥርዐት፥ ሕጉንም አልጠበቅንም። 8“አሁንም ለሙሴ ለባሪያህ እንዲህ ስትል ያዘዝሃትን ነገር አስብ። ብትበድሉም በአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ። 9ወደ እኔ ብትመለሱ ግን፥ ትእዛዜንም ብትጠብቁ፥ ብታደርጓትም ምንም ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ቢበተኑ፥ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ስፍራ አመጣቸዋለሁ። 10“እነዚህም በታላቅ ኀይልህና በብርቱ እጅህ የተቤዥሃቸው ባሪያዎችህና ሕዝብህ ናቸው። 11ጌታ ሆይ፥ ጆሮህ የባሪያህን ጸሎት፥ ስምህንም ይፈሩ ዘንድ የሚወድዱትን የባሪያዎችህን ጸሎት ያድምጥ፤ ዛሬም ለባሪያህ አከናውንለት፤ በዚህም ሰው ፊት ምሕረትን ስጠው።” እኔም ለንጉሡ ጠጅ አሳላፊ ነበርሁ።