1በሠላሳ ሦስተኛውም ኢዮቤልዩ መጀመሪያ እንዲህ ሆነ፤ ለካምና ለሴም ለያፌትም ርስት ልትሆናቸው ከአንደኛው ሱባዔ በመጀመሪያው ዓመት ወደ እነርሱ ከተላክን ከእኛ አንዱ ባለበት ምድርን ሦስት አድርገው ከፈሉአት፤ ልጆቹንም ጠራ፤ እነርሱና ልጆቻቸውም ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ሦስቱ ልጆቹም የሚይዙትን ምድር በዕጣ ከፈለ። 2እጃቸውንም ዘርግተው ከአባታቸው ከኖኅ እጅ መጽሐፉን ተቀበሉ። ርስት አድርጎ የሚይዘው የሴም ዕጣም ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ ለዘለዓለም በመጽሐፍ የምድር መካከል ወጣ። ከአርበኞች ተራራ መካከል ከውኃውም መውጫ ጀምሮ እስከ ጢና ወንዝ ድረስ ወጣ። 3ክፍሉም በዚህ ወንዝ መካከል ወዳለ ወደ ምዕራብ ይደርሳል፤ ይህም ወንዝ ከእርስዋ እስከሚወጣበት እስከ ጥልቁ ውኃ እስኪቀርብ ድረስ ወደዚያ ይሄዳል። ውኃውም ወደ ሚኦት ባሕር ይፈስሳል፤ ይህም ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሄዳል፤ በደቡብም በኩል ያለው ሀገር ሁሉ ለያፌት ደረሰ፤ በሰሜን በኩል ያለውም ሀገር ሁሉ ለሴም ደረሰ። 4ወደ ኮራሶ እስኪቀርብ ድረስ ይሄዳል። ይኸውም ወደ ሰሜን የሚመለከት ሕፅነ ልሳን ነው። ክፍሉም ወደ ታላቁ ባሕር ይደርሳል። ይህች ባሕር ልሳነ ባሕረ ግብፅ ትባላለችና ወደ ሰሜን ወደምታሳይ ወደ ልሳን መግቢያ እስኪቀርብ ድረስ አቅንቶ ይሄዳል። 5ከዚያም ወደ ሰሜን ታዘነብላለች፤ ወደ ታላቁ ባሕር መግቢያ ወደ ውኃውም ዳርቻ ትደርሳለች፤ ወደ አፍራም ግራ ትደርሳለች፤ ግዮን ወደሚባል ፈሳሽ ውኃም እስክትቀርብ ድረስ ትደርሳለች፤ ወደ ግዮንም ውኃ ቀርባ ወደዚህ ፈሳሽ ዳርቻ ትደርሳለች። 6ወደ ኤደን ገነት ወደ ሰሜንም ቀኝ እስክትቀርብ ድረስ ወደ ምሥራቅ ትሄዳለች፤ ከኤዶም ምድር ሁሉ ምሥራቅ፥ ከሀገሩም ሁሉ ምሥራቅ ወደ ምሥራቅ ይመለሳል። ስሙ ራፋ ወደሚባል ተራራ ምሥራቅ እስኪቀርብ ድረስ ይመጣል፤ ወደ ጢና ወንዝ መውጫ ዳርቻም ይወርዳል። 7ይህችም ክፍል ለዘለዓለም ሊይዙአት ለሴምና ለልጆቹ፥ ለልጅ ልጆቹም እስከ ዘለዓለም ድረስ በዕጣ ወጣች። 8ኖኅም ይህ ክፍል የሴምና የልጆቹ ዕጣ ነውና ደስ አለው። “የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፥ እግዚአብሔርም በሴም ማደሪያ ይደር” ብሎአልና በአፉ በትንቢት የተናገረውን ነገር ሁሉ ዐሰበ። የኤዶም ገነት ከከበሩ የከበረች፥ የእግዚአብሔርም ማደሪያ እንደ ሆነች ዐውቆአልና። ደብረ ሲና በምድረ በዳ መካከል ናት፥ ደብረ ጽዮንም በምድር ዕንብርት መካከል ናት፥ እነዚህ ሦስቱ ሁሉ አንዱ በአንዱ አንጻር ለቅድስና ተፈጠሩ። 9በአፉ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲናገር ያደረገውን የአማልክት አምላክ እግዚአብሔርን እስከ ዘለዓለም ድረስ አመሰገነው፤ የተባረከ ክፍልና በረከት ለሴምና ለልጆቹ፥ ለልጅ ልጆቹም እስከ ዘለዓለም ድረስ እንደ ደረሳቸው ዐወቀ። 10የኤዶም ምድር ሁሉ፥ የኤርትራ ባሕር ዳርም ሁሉ፥ የምሥራቅ ምድር ሁሉ በኤርትራና በተራሮቹ በኩል ያለው ሕንድ፥ የባሳን ሀገር ሁሉና የሊባኖስም ሀገር ሁሉ፥ የካፍቱር ደሴቶችና የሳኔር ተራራ ሁሉ፥ አማናና የደቡባዊው አሱር ተራራ፥ የኤላም ሀገር ሁሉ፥ አሱርና ባቢል፥ ሱሳንም ማእዳይና የአራራት ሀገር ሁሉ፥ በደቡብ በኩል ከአለው ከአሱር ተራራ ማዶ የባሕሩ ወደብ እንደ ደረሱት ዐወቀ። የተባረከችና ሰፊ የሆነች፥ በውስጥዋም ያለ ሁሉ እጅግ ያማረ ምድር፤ 11ሁለተኛውም ዕጣ ወደ ግዮን ማዶ በገነት ቀኝ በሰሜን በኩል ለካም ወጣ፥ ወደ ሰሜንም ይደርሳል። ዋዕይ ወደ ጸናበት ተራራም ሁሉ ይደርሳል፤ በአጤል አንጻር ወዳለ ወደ ምዕራብ ይደርሳል። ወደ ማዕከክ ባሕር እስኪቀርብ ድረስም ወደ ምዕራብ ይደርሳል። ይህችውም የሚጠፋው ሁሉ ወደ እርስዋ የሚወርድባት ሀገር ናት። ወደ ደቡብ ወደ ጋዴት ዳርቻ ይወጣል። ወደ ግዮን ወንዝም እስኪቀርብ ድረስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወደ ታላቁ ባሕር ይመጣል። 12ግዮን የተባለው ወንዝም በኤዶም ገነት ቀኝ እስኪቀርብ ድረስ ይሄዳል። ለዘለዓለም ለሚይዛት ለካምና ለልጆቹ፥ ለወገናቸውም እስከ ዘለዓለም ድረስ በዕጣ የወጣች ሀገር ይህች ናት። 13ለያፌትም ሦስተኛው ዕጣ ወጣ። ጢና ወደሚባል ወንዝ ማዶ ወደ ፈሳሾች መውጫ ወደ ደቡብ ወጣ። ወደ ደቡብ ምሥራቅ፥ ወደ ጎግ አውራጃም ሁሉና ወደ ምሥራቃቸው ሁሉ ይደርሳል፥ ከደቡብም ወደ ደቡብ ይደርሳል። ወደ ቄልጥ ተራራና ወደ ደቡብ፥ ወደ ማሉቅም ባሕር ይደርሳል። እስከ ባሕሩ መውጫ ዳርቻ ድረስ ወደ ጋዴት ምሥራቅም ይመጣል። ወደ ፋራ መግቢያም እስኪቀርብ ድረስ ይሄዳል። ወደ ምሥራቅ ወደ ማኡታ ባሕር ወደሚሄደው ወደ አፌራግም ይመለሳል፤ ወደ ውኃው ዳርቻ ወደ ራፋ ተራራ እስኪቀርብም ድረስ ጢና ወደተባለው ወንዝ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ይሄዳል። ደቡብንም ይዞራል። 14ለዘለዓለሙ በርስትነት ዕጣ የሚይዛት፥ ለያፌትና ለልጆቹ፥ ለወገኖቹም የወጣችለት ምድር ይህች ናት። ታላላቅ ደሴቶችዋም አምስት ናቸው። በደቡብ በኩል ያለችውም ሀገር ሰፊ ናት። ነገር ግን የያፌት ሀገር ቀዝቃዛ ናት፤ የካምም ሀገር በረሃ ናት፤ የሴም ሀገር ግን ከውርጭና ከዋዕይ ጋር የተቀላቀለች ናትና ቆላም ደጋም አይደለችም። 15ካም በልጆቹ መካከል አካፈለ። የመጀመሪያው ዕጣም ለኩሽ ወደ ምሥራቅ ወጣ፥ ምዕራቡ ለምጽራይም ወጣ፥ ምዕራቡም ለፉጥ ወጣ፤ ምዕራቡም ለከነዓን ወጣ፤ በምዕራቡም በኩል ባሕር ነበር። 16ሴምም በልጆቹ መካከል አካፈለ። መጀመሪያው ዕጣ ለኤላምና ለልጆቹ እስከ ሕንደኬ ምድር ሁሉ ምሥራቅ እስኪቀርብ ድረስ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ምሥራቅ ወጣ፤ ኤርትራም በእጁ ነበር። የዲዳን ውኃ፥ የሞብሪ ተራሮች፥ የኤላ ሀገር ሁሉ፥ የሱሳም ሀገር ሁሉ፥ በፊርኖክ በኩል ያለው ሁሉ፥ እስከ ኤርትራ ባሕርና እስከ ጢና ወንዝ። 17ለአሶርም ሁለተኛው ዕጣ ወጣ፤ የአሱርና ነነዌ ሀገር ሁሉ፥ ሰናዖርም፥ ሳድም እስከ ሕንደኬ አቅራቢያ ድረስ። ወደ ወድፋ ፈሳሽም ይደርሳል። 18ለአርፋክስድም ሦስተኛው ዕጣ ወጣ። የከላውዴዎን አውራጃ ሀገር ሁሉ፥ ለኤርትራ ባሕር የቀረበው የኤፍራጥስ ምሥራቅም፥ ወደ ግብፅ እስከምትመለከተው እስከ ልሳነ ባሕር አቅራቢያ ድረስ የምድረ በዳው ውኃ ሁሉ፥ የሊባኖስና የሳኔር ሀገር፥ አማናም፥ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ። 19ለአራምም አራተኛው ዕጣ ወጣ፤ በጤግሮስና በኤፍራጥስ መካከል የመስጴጦምያ ሀገር ሁሉ በከላውዴዎን ደቡብ ወዳለ እስከ አሱር አቅራቢያ ድረስ፥ የአራራትም ሀገር ሁሉ የእርሱ ነው። 20ለሉድም አምስተኛው ዕጣ ወጣ፤ የአሱር ተራራ ሁሉ፥ ወደ ታላቁ ባሕር እስኪቀርብ ድረስ የእርሱ ዕጣ ነው። ወደ ወንድሙ ወደ አሶር ምሥራቅም ይደርሳል። 21ያፌትም ምድረ ርስትን በልጆቹ መካከል ከፈለ። መጀመሪያውም ዕጣ ከደቡብ አንጻር ጀምሮ እስከ ጢና ወንዝ ድረስ በምሥራቅ በኩል ለሴሜር ወጣ። በደቡብም በኩል የደቡብ ዙሪያ ሁሉ ለሚአት ባሕር እስኪቀርብ ድረስ ለማጎግ ወጣ። 22ከምዕራቡ ጀምሮ እስከ ደሴቶችና እስከ ደሴቶችም ዳርቻ ድረስ ለሁለቱ ወንድሞቹ ሁሉ ይይዝ ዘንድ ለማዳይ ደረሰ። 23ለኢዮእያንም አራተኛው ዕጣ ወጣ፥ ደሴቱ ሁሉ፥ በሉድም አንጻር ያሉ ደሴቶች ሁሉ። 24ለቶቤልም እስከ ሁለተኛዪቱ ልሳን ድረስ ወደ ሉድ ዕጣ በምትቀርብ በልሳን መካከል አምስተኛው ዕጣ ወጣ። የሁለተኛዪቱም ልሳን አውራጃ እስከ ሦስተኛዪቱ ልሳን ድረስ ነው። 25ለሞሳክም ስድስተኛው ዕጣ ወጣ። እስከ ጋዴር ምሥራቅም እስኪቀርብ ድረስ የሦስተኛዪቱ ልሳን አውራጃ ሁሉ። 26ለቲራስም ሰባተኛው ዕጣ ወጣ። በባሕር መካከል ያሉ፥ ለካም ዕጣ የሚቀርቡ ታላላቁ አራቱ ደሴቶች፤ የክማቱሪ ደሴቶችም በርስትነት ዕጣ ለአርፋክስድ ልጆች ወጡ፤ የኖኅም ልጆች ለልጆቻቸው በአባታቸው በኖኅ ፊት እንዲህ አድርገው ከፈሉ። በዕጣው ያልወጣለትን ክፍል ይይዝ ዘንድ የሚፈልገውን እያንዳንዱን አምሎ ረገመ። 27ሁሉም ይሁን አሉ። ስለሚያጸይፍ ክፉ ኀጢአታቸው ሁሉ፥ ምድርንም በበደልና በርኵሰት፥ በዝሙትና በኀጢአትም ስለ ሞሉአት እግዚአብሔር አምላክ በሰይፍና በእሳት ይፈርድባቸው ዘንድ እስከ ፍርድ ቀን ድረስ በራሳቸውና በልጆቻቸው፥ በዘራቸውም እስከ ዘለዓለም ይሁን አሉ።