ነቢዩ ኤርምያስና ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያ
1ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ በዚያ ዓመት፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ መንግሥት መጀመሪያ፥ በአራተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ሐሰተኛው ነቢይ የገባዖን ሰው የዓዙር ልጅ ሐናንያ በእግዚአብሔር ቤት በካህናትና በሕዝብ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 2“የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር ሰብሬአለሁ። 3የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከዚች ስፍራ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸውን የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደዚህች ስፍራ እመልሳለሁ፤ 4ወደ ባቢሎንም የሄዱትን የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳን ምርኮ ሁሉ ወደዚች ስፍራ እመልሳቸዋለሁ፤ የባቢሎንን ንጉሥ ቀንበር እሰብራለሁና።” 5ነቢዩ ኤርምያስም በካህናቱና በእግዚአብሔር ቤት በቆሙት ሕዝብ ሁሉ ፊት ለሐሰተኛው ነቢይ ለሐናንያ ተናገረ። 6ነቢዩም ኤርምያስ እንዲህ አለ፥ “አሜን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርግ፤ የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ፥ ምርኮውንም ሁሉ ከባቢሎን ወደዚህ ስፍራ በመመለስ እግዚአብሔር የተናገርኸውን ትንቢት ይፈጽም። 7ነገር ግን በጆሮህና በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ የምናገረውን የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ 8ከጥንት ከእኔና ከአንተ በፊት የነበሩ ነቢያት በብዙ ሀገርና በታላላቅ መንግሥታት ላይ ስለ ሰልፍና ስለ ክፉ ነገር ስለ ቸነፈርም ትንቢት ተናገሩ። 9ስለ ሰላም ትንቢት የተናገረ ነቢይ ትንቢቱ በደረሰ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በእውነት የላከው ነቢይ እንደ ሆነ ይታወቃል።” 10ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያም በሕዝቡ ሁሉ ፊት ቀንበሩን ከነቢዩ ከኤርምያስ አንገት ወስዶ ሰበረው። 11ሐናንያም በሕዝቡ ሁሉ ፊት፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንግዲህ በሁለት ዓመት ውስጥ የባቢሎንን ንጉሥ የናቡከደነፆርን ቀንበር ከአሕዛብ ሁሉ አንገት እሰብራለሁ” አለ። ነቢዩ ኤርምያስም መንገዱን ሄደ። 12ሐናንያም ቀንበሩን ከነቢዩ ኤርምያስ አንገት ከሰበረ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 13“ሂድ፥ ለሐናንያ እንዲህ ብለህ ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ የእንጨትን ቀንበር ሰብረሃል፤ እኔ ግን በእርሱ ፋንታ የብረትን ቀንበር እሠራለሁ። 14የእስራኤልም አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር ይገዙለት ዘንድ የብረትን ቀንበር በእነዚህ አሕዛብ ሁሉ አንገት ላይ አድርጌአለሁ፤ እነርሱም ይገዙለታል፤ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ።” 15ነቢዩም ኤርምያስ ሐሰተኛውን ሐናንያን፥ “ሐናንያ ሆይ ስማ፤ እግዚአብሔር አልላከህም፤ ነገር ግን ይህ ሕዝብ በሐሰት እንዲታመን አድርገሃል። 16ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ከገጸ ምድር አስወግድሃለሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፅን ተናግረሃልና በዚህ ዓመት ትሞታለህ” አለው። 17ሐሰተኛው ነቢይ ሐናንያም በዚያው ዓመት በሰባተኛው ወር ሞተ።