ኤርምያስ የተሸከመው ቀንበር
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም መንግሥት መጀመሪያ ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ መጣ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰንሰለትና ቀንበር ሥራ፤ በአንገትህም ላይ አድርግ፤ 3ወደ ይሁዳ ንጉሥም ወደ ሴዴቅያስ፥ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡት መልእክተኞች እጅ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ፥ ወደ ሞዓብም ንጉሥ፥ ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ፥ ወደ ጢሮስም ንጉሥ፥ ወደ ሲዶናም ንጉሥ ላክ።” 4ለጌቶቻቸው እንዲነግሩ እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፥ “የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለጌቶቻችሁ እንዲህ በሉ፦ 5ምድሪቱን፥ በምድር ፊት ላይ ያሉትን ሰዎችንና እንስሶችን በታላቅ ኀይሌና በተዘረጋችው ክንዴ ፈጥሬአለሁ፤ ለዐይኔም መልካም ለሆነው እሰጣታለሁ። 6አሁንም ምድርን ሁሉ ለባሪያዬ ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ፤ ያገለግሉትም ዘንድ የምድረ በዳ አራዊትን ደግሞ ሰጥቼዋለሁ። 7የገዛ ራሱም ምድር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አሕዛብ ሁሉ ለእርሱና ለልጁ ለልጅ ልጁም ይገዛሉ፤ በዚያን ጊዜም ብዙ አሕዛብና ታላላቆች ነገሥታት ለእርሱ ይገዙለታል። 8“ለባቢሎን ንጉሥም ለናቡከንደነፆር የማይገዛውን፥ ከባቢሎንም ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የማያደርገውን ሕዝብና መንግሥት፥ ያን ሕዝብ በእጁ እስካጠፋው ድረስ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም እቀጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 9እናንተ ግን፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የሐሰት ነቢያቶቻችሁንና ምዋርተኞቻችሁን፥ ሕልም ዐላሚዎቻችሁንና ባለ ራእዮቻችሁን፥ መተተኞቻችሁንም አትስሙ፤ 10ከምድራችሁ እንዲያርቁአችሁ፥ እኔም እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተም እንድትጠፉ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገሩላችኋልና። 11ነገር ግን ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገቱን ዝቅ የሚያደርገውንና የሚገዛለትን ሕዝብ በሀገሩ ላይ እተወዋለሁ፤ እርሱም ያርሳታል፤ ይቀመጥባትማል።” 12ለይሁዳ ንጉሥ ለሴዴቅያስም ይህን ቃል ሁሉ ተናገርሁ፥ “ከባቢሎን ንጉሥ ቀንበር በታች አንገታችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ለእርሱና ለሕዝቡም ተገዙላቸው በሕይወትም ኑሩ። 13ለባቢሎን ንጉሥ ይገዛ ዘንድ እንቢ ስላለ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ፥ አንተና ሕዝብህ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ለምን ትሞታላችሁ? 14ሐሰተኛን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፦ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም የሚሉአችሁን የነቢያትን ቃል አትስሙ። 15እኔ አልላክኋቸውምና፤ ነገር ግን እኔ እንዳሳድዳችሁ፥ እናንተና ትንቢት የሚናገሩላችሁ ነቢያትም እንድትጠፉ በስሜ ሐሰተኛ ትንቢትን ይናገራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።” 16ለካህናትም ለዚህም ሕዝብ እንዲህ ብዬ ተናገርሁ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሐሰተኛውን ትንቢት ይናገሩላችኋልና፦ የእግዚአብሔር ቤት ዕቃ በቅርብ ጊዜ ከባቢሎን ይመለሳል የሚሉአችሁን የነቢያቶቻችሁን ቃል አትስሙ። 17እነርሱን አትስሙ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ተገዙ፤ በሕይወትም ኑሩ፤ ይህችስ ከተማ ስለ ምን ባድማ ትሆናለች? 18እነርሱ ግን ነቢያት ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በእነርሱ ዘንድ ቢገኝ፥ በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት፥ በኢየሩሳሌምም የቀሩት ዕቃዎች ወደ ባቢሎን እንዳይሄዱ ወደ ሠራዊት ጌታ ወደ እግዚአብሔር ይማለሉ።” 19ስላልወሰዳቸው ዓምዶች፥ ስለ ባሕሩም፥ ስለ መቀመጫዎቹም፥ በዚች ከተማ ስለ ቀሩት ዕቃዎች ሁሉ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ 20“የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንንና የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን አለቆች ሁሉ ማርኮ ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ባፈለሳቸው ጊዜ፥ 21በእግዚአብሔር ቤትና በይሁዳ ንጉሥ ቤት፥ በኢየሩሳሌምም ስለ ቀሩት ዕቃዎች የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 22ወደ ባቢሎን ይወሰዳሉ፤ እስከምጐበኛቸው ቀን ድረስ በዚያ ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በዚያን ጊዜም ትወጣላችሁ፤ ወደዚህም ስፍራ ትመለሳላችሁ።”