1ጌታ ሆይ፥ ነገራችንን ማን ያምነናል? የእግዚአብሔርስ ክንድ ለማን ተገልጦአል? 2ነገራችን በፊቱ እንደ ሕፃን፥ በደረቅ መሬትም እንዳለ ሥር ሆነ፤ መልክና ውበት የለውም፤ እነሆ፥ አየነው፤ ደም ግባት የለውም፤ ውበትም የለውም። 3መልኩም የተናቀ፥ ከሰውም ልጆች ሁሉ የተዋረደ፥ የተገረፈ ሰው፥ መከራንም የተቀበለ ነው፤ ፊቱንም መልሶአልና አቃለሉት፥ አላከበሩትምም። 4እርሱ ግን በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤ እኛም እንደ ታመመ፥ እንደ ተገረፈም ቈጠርነው። 5እርሱ ግን ስለ ኀጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። 6እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም ስለ ኀጢአታችን ለሞት አሳልፎ ሰጠው። 7እርሱ ግን በመከራው ጊዜ አፉን አልከፈተም፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። 8በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዷልና ልደቱን ማን ይናገራል? ስለ ሕዝቤ ኀጢአት ለሞት ደረሰ። 9ክፉዎችንም ስለ መቃብሩ፥ ባለጸጎችንም ስለ ሞቱ እሰጣለሁ፤ ኀጢአትን አላደረገምና፥ ከአፉም ሐሰት አልተገኘበትምና። 10እግዚአብሔር ከግርፋቱ ያነጻው ዘንድ ፈቀደ፤ ስለ ኀጢአት መሥዋዕትን ብታቀርቡ ሰውነታችሁ ረዥም ዕድሜ ያለውን ዘር ታያለች። 11እግዚአብሔርም ከሰውነቱ ሕማምን ያርቅ ዘንድ ይወዳል፤ ብርሃንንም ያሳየዋል፤ በጥበቡም ይለየዋል፤ ለጽድቅና ለበጎ ነገር የሚገዛውን ጻድቁን ያጸድቀዋል። የብዙዎችንም ኀጢአታቸውን እርሱ ይደመስሳል። 12ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፤ ከኀያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዐመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ኀጢአታቸውም ተሰጠ።