እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንደታደጋት
1ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፤ ጽዮን ሆይ፥ ኀይልሽን ልበሺ፤ አንቺም ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ ወደ አንቺ አያልፍምና ክብርሽን ልበሺ። 2ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትቢያን አራግፊ፤ ተነሺ፥ ተቀመጪ፤ ምርኮኛዪቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የአንገትሽን እስራት ፍቺ። 3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በከንቱ ተሸጣችሁ ነበር፤ ያለ ወርቅም እቤዣችኋለሁ።” 4ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሕዝቤ አስቀድሞ ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚያም በስደት ኖሩ፤ ከዚያም ወደ አሦር በግድ ተወሰዱ። 5ሕዝቤ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አቆማችሁ?” ይላል እግዚአብሔር፤ “ታደንቃላችሁ፤ ትጮሃላችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ስሜም በእናንተ ምክንያት በአሕዛብ ዘንድ ሁልጊዜ ይሰደባል። 6ስለዚህ ሕዝቤ ስሜን ያውቃል፤ የምናገርና ያለሁ እኔ እንደ ሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ።” 7ሰላምን የሚያወራ፥ መልካም የምሥራችንም የሚናገር፥ መድኀኒትንም የሚያወራ፥ ጽዮንንም፥ “አምላክሽ ነግሦአል” የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው። 8እነሆ፥ የሚጠብቁሽ ሰዎች ድምፅ ከፍ ከፍ ይላልና፥ እግዚአብሔርም ጽዮንን ይቅር ባላት ጊዜ ዐይን በዐይን ይተያያሉና በአንድነት በቃላቸው ደስ ይላቸዋል። 9የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ደስ ይበላቸው፤ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ኢየሩሳሌምን አድኖአታልና። 10እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፤ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን ማዳን ያያሉ። 11እናንተ የእግዚአብሔርን ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፤ እልፍ በሉ፤ ከዚያ ውጡ፤ ርኩስን ነገር አትንኩ፤ ከመካከልዋ ውጡ፤ ራሳችሁን ለዩ። 12እግዚአብሔር በፊታችሁ ይሄዳልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይሰበስባችኋልና በችኮላ አትወጡም፤ በመኮብለልም አትሄዱም።