የምስጋና መዝሙር
1በዚያም ቀን እንዲህ ትላለህ፥ “አቤቱ፥ ተቈጥተኸኛልና፥ ቍጣህንም ከእኔ መልሰሃልና፥ ዳግመኛም ይቅር ብለኸኛልና አመሰግንሃለሁ። 2እነሆ፥ አምላኬ መድኀኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ክብሬና ዝማሬዬ ነው፤ መድኀኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜአለሁ፤ አልፈራምም።” 3ውኃውንም ከሕይወት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ። 4በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ፥ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ክብሩን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ አስታውሱ። 5ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ስም ዘምሩ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ። 6አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤ የእስራኤል ቅዱስ በመካከልሽ ከፍ ከፍ ብሎአልና።”