ሰላም የሰፈነበት መንግሥት
1ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከግንዱ ይወጣል። 2የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኀይል መንፈስ፥ የዕውቀትና የእውነት መንፈስ ያርፍበታል። 3እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ይሞላበታል፤ በፍርድ አያዳላም፤ በነገርም አይከራከርም፤ 4ነገር ግን ለድሆች በጽድቅ ይፈርዳል፤ ለምድርም የዋሆች በቅንነት ይበይናል፤ በአፉም ቃል ምድርን ይመታል፤ በከንፈሩም እስትንፋስ ኀጢአተኛውን ያጠፋዋል። 5ወገቡን በጽድቅ ይታጠቃል፤ እውነትንም በጎኑ ይጐናጸፋል። 6ተኵላ ከበግ ጠቦት ጋር ይሰማራል፤ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና በሬ የአንበሳ ደቦልም በአንድነት ይሰማራሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። 7ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያድጋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። 8የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጕድጓድና በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። 9እነርሱም አይጐዱትም፤ በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ ማንንም አይጐዱም፤ አያጠፉምም፤ ብዙ ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና።
የእስራኤል ከስደት መመለስ
10በዚያም ቀን የእሴይ ሥር ይቆማል፤ የተሾመውም የአሕዛብ አለቃ ይሆናል፤ አሕዛብም በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ፤ ማረፊያውም የተከበረ ይሆናል። 11በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ከአሦርና ከግብፅ፥ ከባቢሎንና ከኢትዮጵያ፥ ከኤላሜጤን፥ ከምሥራቅና ከምዕራብ ለቀሩት ለሕዝቡ ቅሬታ ይቀና ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ገና እጁን ይገልጣል። 12ለአሕዛብም ምልክትን ያቆማል፤ ከእስራኤልም የቀሩትን ይሰበስባል፤ ከይሁዳም የተበተኑትን ከአራቱ የምድር ማዕዘኖች ያከማቻል። 13የኤፍሬምም ቅናት ይሻራል፤ የይሁዳም ጠላቶች ይጠፋሉ፤ ኤፍሬምም በይሁዳ አይቀናም፤ ይሁዳም ኤፍሬምን አያስጨንቅም። 14በባሕርም በኩል በፍልስጥኤማውያን መርከቦች ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፤ የምሥራቅ ሰዎችንና ኤዶምያስን በአንድነት ይዘርፋሉ፤ በሞዓብ ላይ ቀድመው እጃቸውን ይዘረጋሉ፤ የአሞንም ልጆች ቀድመው ለእነርሱ ይታዘዛሉ። 15እግዚአብሔርም የግብፅን ባሕር ያደርቃል፤ በኀይለኛም ነፋስ እጁን በወንዙ ላይ ያነሣል፤ ሰባት ፈሳሾችንም ይመታል፤ ሰዎችም በጫማቸው እንዲሻገሩ ያደርጋቸዋል። 16ከግብፅም በወጣ ጊዜ ለእስራኤል እንደ ነበረ፥ በአሦር ለቀረው ለሕዝቡ ጎዳና ይሆናል።