ስለ ሰንበት
1እንግዲህ አንፍራ፤ ወደ ዕረፍቱም እንድንገባ ትእዛዙን አንተው፤ ከእናንተም ምንአልባት በተለመደ ስሕተት የሚገኝና የሚጸና ቢኖር ወደ ዕረፍቱ እንዲገባ የሚተዉት አይምሰለው። 2ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛም የምሥራች ተሰብኮልናል፤ ነገር ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። 3ሥራዉ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፥ “እንግዲህ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቍጣዬ ማልሁ” እንዳለ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። 4ስለ ሰባተኛውም ቀን፥ “እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሎአልና። 5ዳግመኛም፥ “ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” ብሎአል። 6እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ መንገድ ስለ ነበራቸው ቀድሞም የምሥራች የተሰበከላቸው ባለ መታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፦ 7“ዛሬ ቃሉን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ፤” በፊት እንደ ተባለ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፥ “ዛሬ” ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። 8ኢያሱ አሳርፎአቸው ቢሆን ኖሮስ፥ ከብዙ ዘመን በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረም ነበር። 9እንኪያስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚገቡበት ጸንቶ የሚኖር ዕረፍት እንዳለ ታወቀ። 10ወደ ዕረፍቱ የገባስ እግዚአብሔር ከሥራው እንደ ዐረፈ፥ እነሆ፥ እርሱ ከሥራው ሁሉ ዐረፈ። 11እንግዲህ እንደ እነዚያ እንደ ካዱት እንዳንወድቅ፥ ወደ ዕረፍቱ እንገባ ዘንድ እንፋጠን። 12የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፤ የሚሠራም ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍም ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስንም፥ ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፤ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል። 13እኛን በሚቈጣጠር በእርሱ በዐይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም።