ወደ ገላትያ ሰዎች 3
የገላትያን ሰዎች ስለ መገሠጹ
1እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ ለዐይን በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ? እርሱም እንዲሰቀል አስቀድሞ የተጻፈለት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 2በእናንተ ዘንድ ይህን ብቻ ላውቅ እወድዳለሁ፤ መንፈስ ቅዱስን የተቀበላችሁ የኦሪትን ሥራ በመሥራት ነውን? ወይስ ሃይማኖትን በመስማት? 3እንዲህን ሰነፎች ናችሁን? የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከጀመራችሁ በኋላ የሥጋን ሕግ ልትሠሩ ትመለሳላችሁን? 4ይህን ያህል መከራ ተቀብላችሁ፥ ለከንቱ አደረጋችሁት። 5እርሱ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጣችሁ፥ ኀይልንም የሚያደርግላችሁ የኦሪትን ሥራ በመሥራት ነውን? ወይስ ሃይማኖትን በመስማት ነው?
ስለ አብርሃም እምነትና ተስፋው
6አብርሃም በእግዚአብሔር እንደ አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ እንደ ተቈጠረለት፥ 7እንግዲህ ያመኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ ታውቃላችሁ። 8እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቃቸው መጽሐፍ አስቀድሞ ገልጦአልና፤ አሕዛብም ሁሉ በእርሱ እንዲባረኩ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋ ሰጠው። 9አሁንም የሚያምኑ ከአመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። 10በኦሪት ሕግ ያሉ ሁሉ በእርግማን ውስጥ ይኖራሉ፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በዚህ በኦሪት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈውን ሁሉ የማይፈጽምና የማይጠብቅ ርጉም ይሁን።” 11የኦሪትን ሥራ በመሥራትስ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደማይጸድቁ ይታወቃል፤ “ጻድቅ ግን በእምነት ይድናል” ተብሎ ተጽፎአል። 12ኦሪትስ ሠርቶ የፈጸመ ይኖርበታል እንጂ በእምነት የሚያጸድቅ አይደለም። 13እኛንስ ክርስቶስ ስለ እኛ የኦሪትን መርገም በመሸከሙ ከኦሪት መርገም ዋጅቶናል፤ መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “በእንጨት ላይ የተሰቀለ ሁሉ ርጉም ነው።” 14እኛ በክርስቶስ አምነን የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ እንድናገኝ የአብርሃም በረከት በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አሕዛብ ይመለስ ዘንድ።
ስለ ኦሪትና ስለ ተስፋው
15ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እንናገራለን፤ ሰውም እንኳን የጸናውን ኪዳን አይንቅም አይጨምርበትምም። 16እግዚአብሔርም ለአብርሃም፥ “ለአንተና ለዘርህ” ብሎ ተስፋ ሰጠው፤ ለብዙዎች እንደሚናገር አድርጎ ለአንተና ለዘሮችህ አላለውም፤ ለአንድ እንደሚናገር አድርጎ፥ “ለዘርህ” አለው እንጂ ይኸውም ክርስቶስ ነው። 17እንግዲህ እንዲህ እላለሁ፦ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ይህ ኪዳን ጽኑዕ ነው፤ ከዚህም በኋላ በአራት መቶ ሠላሳ ዓመት ኦሪት መጣች፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል አይደለም። 18መውረስ የኦሪትን ሕግ በመሥራት ከሆነ እንግዲህ በሰጠው ተስፋ አይደለማ፤ እነሆ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለአብርሃም ተስፋውን ሰጠው። 19ታዲያ ኦሪት ለምን ተሠራች? ኦሪትስ ኀጢአትን ታበዛት ዘንድ፥ ተስፋ ያደረገለት ያ ዘር እስኪመጣ ድረስ፥ በመላእክት በኩል በመካከለኛው እጅ ወረደች። 20መካከለኛው ግን ማንም አይደለም፤ አንድ እግዚአብሔር ነው እንጂ። 21እንግዲህ ኦሪት እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ልትከለክል መጣችን? አይደለም፤ ማዳን የሚቻለው ሕግ ተሠርቶ ቢሆንማ፥ በእውነት በዚያ ሕግ ጽድቅ በተገኘ ነበር። 22ነገር ግን ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ይሆን ዘንድ፥ ያመኑትም ያገኙት ዘንድ፥ መጽሐፍ ሁሉን በኀጢአት ዘግቶታል።
ስለ ሃይማኖት መምጣት
23እምነት ሳይመጣ ኦሪት ጠበቀችን፤ ወደሚመጣውም እምነት መራችን። 24እንግዲህ ኦሪት በእርሱ በማመን እንጸድቅ ዘንድ ወደ ክርስቶስ መሪ ሆነችን። 25እንግዲህ እምነት ከመጣች መሪ አንሻም። 26በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናልና። 27በክርስቶስ የተጠመቃችሁ እናንተማ ክርስቶስን ለብሳችኋል። 28በዚህም አይሁዳዊ፥ ወይም አረማዊ የለም፤ ገዢ፥ ወይም ተገዢ የለም፤ ወንድ፥ ወይም ሴት የለም፤ ሁላችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ናችሁና። 29ለኢየሱስ ክርስቶስ ከሆናችሁም እንግዲህ ተስፋውን የምትወርሱ የአብርሃም ዘር እናንተ ናችሁ።