ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6
ስለ ልጆችና ስለ ወላጆች
1ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታችን ታዘዙ፤ ይህ የሚገባ ነውና። 2በሕግም ተስፋ ያለው የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው፥ “አባትህንና እናትህን አክብር፤ 3መልካም ይሆንልህ ዘንድ፥ በምድር ላይም ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ።” 4እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በእግዚአብሔር ተግሣጽና ምክር አሳድጉአቸው እንጂ አታስቈጡአቸው።
ስለ አገልጋዮችና ስለ አሳዳሪዎቻቸው
5አገልጋዮችም በሥጋችሁ ለሚገዙአችሁ ጌቶቻችሁ በፍርሀትና በመደንገጥ፥ በሰፊ ልብም ለክርስቶስ እንደምትገዙ ታዘዙ። 6የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሮች እንጂ ለሰው ደስ እንደሚያሰኝ ለታይታ አይደለም። 7ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንደምትገዙ በፍጹም ሰውነታችሁ በፍቅርና በበጎ ፈቃድ ተገዙላቸው። 8ጌታም ቢሆን፥ አገልጋይም ቢሆን መልካም ያደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ እንደሚያገኝ ታውቃላችሁና። 9እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ቍጣችሁን እያበረዳችሁ፥ በደላቸውንም ይቅር እያላችሁ፥ ትክክለኛውን አድርጉላቸው፤ ፊት አይቶ የማያዳላ ጌታ በእነርሱና በእናንተ ላይ በሰማይ እንደ አለ ታውቃላችሁና።
ሃይማኖትና ፍጹም ተጋድሎ
10እንግዲህስ ወዲህ በእግዚአብሔርና በኀይሉ ጽናት በርቱ። 11የሰይጣንን ተንኰል መቋቋም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ። 12ሰልፋችሁ፦ ከጨለማ ገዦች ጋርና ከሰማይ በታች ካሉ ከክፉዎች አጋንንት ጋር ነው እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ጋር አይደለምና። 13ስለዚህም በክፉ ቀን መቃወም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ጋሻ ያዙ፤ እንድትጸኑም በሁሉ የተዘጋጃችሁ ሁኑ። 14እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ ቁሙ፤ የጽድቅንም ጥሩር ልበሱ። 15የሰላም ወንጌል ኀይልንም ተጫምታችሁ ቁሙ። 16ከዚህም ሁሉ ጋር የሚንበለበሉ የክፉን ፍላፃዎች ሁሉ ማጥፋት እንድትችሉ የእምነትን ጋሻ አንሡ። 17የመዳንንም የራስ ቍር በራሳችሁ ላይ ጫኑ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ሰይፍ ያዙ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 18በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁልጊዜ ትጉ፤ 19ለእኔም፦ ቃልን እንዲሰጠኝ፥ አፌንም ከፍቼ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንድናገር ጸልዩልኝ። 20ስለ ወንጌልም በእስራት መልእክተኛ የሆንሁ፦ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ጸልዩ። 21እናንተም ዜናዬን እንድታውቁ የምንወደው ወንድማችን የታመነ የእግዚአብሔር አገልጋይ ቲኪቆስ የምሠራውን ሁሉ ያስረዳችኋል። 22ዜናዬን ታውቁ ዘንድ፥ ልባችሁም ይጽናና ዘንድ፥ ስለዚህ ወደ እናንተ ላክሁት። 23ከአባታችን ከእግዚአብሔር አብ፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስም ከእምነት ጋር ሰላምና ፍቅር ለወንድሞቻችን ይሁን። 24ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለ መጥፋት ከሚወዱት ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን። አሜን።