እግዚአብሔርን መምሰል
1እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ። 2ክርስቶስ እንደ ወደዳችሁ፥ ራሱንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ የሚሆን መሥዋዕትና ቍርባን አድርጎ እንደ ሰጠላችሁ በፍቅር ተመላለሱ። 3ነገር ግን ለቅዱሳን እንደሚገባቸው፥ ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም ቅሚያ አይሰማባችሁ። 4የሚያሳፍር ነገርም፥ የስንፍና ነገርም፥ ወይም የማይገባ የዋዛ ነገር በእናንተ ዘንድ አይሁን፤ ማመስገን ይሁን እንጂ። 5ሴሰኛ፥ ወይም ኀጢአተኛ፥ ወይም ቀማኛ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ሁሉ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ መንግሥት ዕድል ፋንታ እንደሌለው ይህን ዕወቁ። 6በከንቱ ነገርም የሚያስታችሁ አይኑር፤ በእርሱ ምክንያት በከሓዲዎች ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መዓት ይመጣልና። 7እንግዲህ አትምሰሉአቸው። 8ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ ዛሬ ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችኋል። እንግዲህስ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ። 9የብርሃን ፍሬው በጎ ሥራና እውነት፥ ቅንነትም ሁሉ ነውና። 10እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ። 11የሥራ ፍሬ ከሌላቸው፥ ሁለንተናቸውም ጨለማ ከሆነ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ገሥጹአቸው እንጂ። 12በስውር የሚሠሩት ሥራ ለመናገር የሚያሳፍር ነውና። 13ነገር ግን በብርሃን የተገለጠ ሁሉ ይታወቃል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። 14“የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሎአልና። 15እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ። 16ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት። 17ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ። 18መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ። 19መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም። 20ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ።
ስለ ትሕትናና የቤተ ሰብእ አመራር
21እግዚአብሔርን በመፍራት ለባልንጀሮቻችሁ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ። 22ሴቶችም ለጌታችን እንደሚታዘዙ ለባሎቻቸው ይታዘዙ። 23ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስዋ አዳኝዋም እንደ ሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና። 24ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ፥ እንዲሁም ሴቶች ለባሎቻቸው በሁሉ ይታዘዙ። 25ወንዶችም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት፥ ራሱንም ስለ እርስዋ ቤዛ አድርጎ እንደ ሰጠላት ሚስቶቻቸውን ይውደዱ። 26በውኃ ጥምቀትና በቃሉ ይቀድሳትና ያነጻት ዘንድ፥ 27የነጻችና የተቀደሰች ትሆን ዘንድ እንጂ በላይዋ እድፈት ወይም ርኵሰት እንዳያገኝባት፥ ቤተ ክርስቲያኑን ለእርሱ የከበረች ያደርጋት ዘንድ፤ 28እንዲሁም ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው ይውደዱ፤ ሚስቱንም የወደደ ራሱን ወደደ። 29ከቶ ሥጋውን መጥላት የሚቻለው የለም፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ መገባት መግቡ፤ ጠብቁም። 30እኛ የአካሉ ሕዋሳት ነንና። 31“ስለዚህም ወንድ አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ።” 32ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ። 33እንግዲያስ እናንተም ሁላችሁ እንዲሁ ሚስቶቻችሁን እንደ ራሳችሁ ውደዱ፥ ሴትም ባልዋን ትፍራው።