ትንቢተ ዓሞጽ 2
ስለ ሞዓብ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 2በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የከተሞችዋንም መሠረቶች ትበላለች፤ ሞዓብም በድካምና በውካታ፥ በመለከትም ድምፅ ይሞታል፤ 3ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፤ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ” ይላል እግዚአብሔር።
ስለ ይሁዳ
4እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእግዚአብሔርን ሕግ አፍርሰዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ከንቱ ነገር አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 5በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም መሠረቶች ትበላለች።”
የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ላይ
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ጻድቁን በብር፥ ችጋረኛውንም ምድርን በሚረግጡበት አንድ ጥንድ ጫማ ሸጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 7የድሆችን ራስ ይቀጠቅጣሉ፤ የትሑታንንም ፍርድ ያጣምማሉ፤ የአምላካቸውንም ስም ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤ 8ልብሳቸውንም አስረው ለመሥዊያው መጋረጃ ያደርጋሉ፤ በአምላካቸውም ቤት የቅሚያ ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። 9እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ወይራ ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። 10የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። 11ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ለእኔ የተለዩትን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህ እንደዚህ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር። 12“እናንተ ግን ለእኔ የተለዩትን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም፥ “ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ ከለከላችኋቸው። 13“ስለዚህ ሠረገላ ብርዑን እንዲያደቅ፥ በበታቻችሁ ባለ መሬት እኔ አደቅቃችኋለሁ። 14የሚሮጥ ሰው ማምለጥ አይችልም፤ ኀይለኛውም በብርታቱ አይዝም፤ አርበኛውም ነፍሱን አያድንም። 15ቀስተኛውም አይቆምም፤ ፈጣኑም አያመልጥም፤ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤ 16ልበ ሙሉው ኀይለኛም በኀይሉ አይተማመንም፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል” ይላል እግዚአብሔር።