ትንቢተ ዓሞጽ 1
1በቴቁሔ በላም ጠባቂዎች መካከል የነበረ አሞጽ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ዘመን፥ በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን፥ የምድር መናወጥ ከሆነበት ከሁለት ዓመት በፊት ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል ይህ ነው። 2እንዲህም አለ፥ “እግዚአብሔር ከጽዮን ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ ከኢየሩሳሌምም ሆኖ ቃሉን ይሰጣል፤ የእረኞችም ማሰማሪያዎች ያለቅሳሉ፤ የቀርሜሎስም ራስ ይደርቃል።”
ስለ ቂር
3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የገለዓድን ነፍሰ ጡሮች በብረት መጋዝ ሰንጥቀዋቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የደማስቆ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 4በአዛሄል ቤት ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የወልደ አዴርንም መሠረቶች ትበላለች። 5የደማስቆንም ቍልፎች እሰብራለሁ፤ በአዎን ሸለቆ የሚኖሩትንም ሰዎች አጠፋለሁ፤ የካራን ሰዎች ወገኖችንም እቈራርጣለሁ፤ የሶርያ ሕዝብም ወደ ቂር ይማረካሉ፤” ይላል እግዚአብሔር።
ስለ ፍልስጥኤም
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በኤዶምያስ ይዘጉባቸው ዘንድ የሰሎሞንን ምርኮ ማርከዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጋዛ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 7በጋዛ ቅጥር ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ መሠረቶችዋንም ትበላለች። 8የአዛጦን ነዋሪዎችን አጠፋለሁ፤ የአስቀሎናም ሕዝብ ይጠፋለሁ፤ እጄንም በአቃሮን ላይ እመልሳለሁ፤ ከፍልስጥኤማውያን የቀሩትም ይጠፋሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ስለ ጢሮስ
9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የሰሎሞን ምርኮኞችን በኤዶምያስ ዘግተዋልና፥ የወንድሞችንም ቃል ኪዳን አላሰቡምና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የጢሮስ ኀጢአት አልመለስላቸውም። 10በጢሮስ ቅጥር ላይ እሳትን አሰድዳለሁ፤ መሠረቶችዋንም ትበላለች።”
ስለ ኤዶም
11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦“ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ በምድር ላይም ማኅፀንን አርክሶአልና፥ የሚዘልፈውንና የሚያስደነግጠውን በርብሮአልና፥ መዓቱንም ለዘለዓለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። 12በቴማን ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የቅጥርዋንም መሠረቶች ትበላለች።”
ስለ አሞን
13እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ዳርቻቸውን ያሰፉ ዘንድ የገለዓድን ነፍሰ ጡሮች ቀድደዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የአሞን ልጆች ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስም። 14በራባ ቅጥር ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ በጦርነት ቀን በጩኸት መሠረቶችዋን ትበላለች፤ በፍጻሜዋም ቀን ትናወጣለች። 15ንጉሦቻቸውን፥ አለቆቻቸውንና ካህኖቻቸውን በአንድነት ይማርኳቸዋል፥” ይላል እግዚአብሔር።