ዝነኞች የዳዊት ኀያላን
8የዳዊት ኀያላን ስም ይህ ነው። የሦስተኛው ክፍል አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፤ ጎራዴውን መዝዞ ስምንት መቶ ያህል ጭፍሮችን በአንድ ጊዜ የገደለ አሶናዊው አዲኖን ነበረ። 9ከእርሱም በኋላ የዳዊት የአጎቱ ልጅ የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፤ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከነበሩ ከሦስቱ ኀያላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ። 10የእስራኤልም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እርሱ ተነሥቶ እጁ እስከሚደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኀኒት አደረገ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ የሞቱትን ለመግፈፍ ብቻ ተመለሱ። 11ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሴሜይ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም በቴሪያ ተሰበሰቡ። በዚያም ምስር የሞላበት የእርሻ ክፍል ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። 12እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኀኒት አደረገ። 13ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ወደ ቃሶን ወደ ዳዊት ወደ አዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 14በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ። 15ዳዊትም፥ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ?” ብሎ ተመኘ። ያንጊዜም የፍልስጥኤማውያን ኀይል በቤተ ልሔም ነበረ። 16ሦስቱም ኀያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሰንጥቀው ሄዱ፤ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፈሰሰው። 17“አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ ነፍሳቸውን ሰጥተው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኀያላንም ያደረጉት ይህ ነው። 18የሶርህያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበር። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ ስሙም በሦስቱ ዘንድ ተጠርቶ ነበር። 19እርሱም ከሦስቱ ይልቅ የከበረ ነበር፤ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። 20በቀበስሄል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የአርኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። 21እርሱም ልዩ የሆነውን ግብፃዊ ሰው ገደለ፤ ግብፃዊውም በእጁ ዛቢያው እንደ ድልድይ ዕንጨት የሆነ ጦር ነበረው፤ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፤ ከግብፃዊውም እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው። 22የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኀያላን ተጠርቶ ነበር። 23ከሦስቱም ይልቅ የከበረ ነበረ፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም ትእዛዝ አስከባሪ አድርጎ ሾመው። 24የዳዊት ኀያላንም ስማቸው ይህ ነው። የኢዮአብ ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፤ የቤተ ልሔም ሰው የአጎቱ የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ 25አሮዳዊው ሴሜይ፥ ሔሮዳዊው አልያቃ፥ 26ፈልጣዊው ሴሌ፥ የቴቁሓዊው የኤስካ ልጅ ዔራስ፥ 27ከአስቲጡ ልጆች ወገን የሚሆን አናቶታዊው አብዔዜር፥ 28የኤሎንያ ሰው ኤላን፥ የፋጤ ሰው ናኤሬት፥ 29የአንጢፋ ሰው የቦአና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን ከጌብዓ የረባይ ልጅ ኢታይ፥ 30ኤፍራታዊው በናያስ፥ የአብሪስ ሰው አሶም፥ 31ዓረባዊው አቤዔልቦን፥ አልሞናዊው ኤማሱኖስ፥ 32አሴሌቦናዊው ኤልያሕባ፥ የአሶን ልጅ ዮናታን፥ 33አሮዳዊው ሳምናን፥ የሓተራዊው የሶሬ ልጅ አምናን፥ 34የመካኪ ልጅ የአሶብ ልጅ ኤላፍላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥ 35ቀርሜሎሳዊው አሰሬ፥ አረባዊው ኤፌዎ፥ 36የናታን ልጅ ኤአኪ፥ ከገዓድ ልጆች ወገን ማሶባ፥ 37አሞናዊው ኤልዩ፥ የሶርህያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ጌሎሬ፥ 38ኤተራዊው ዒራስ፥ ኢታናዊው ጋሬብ፥ 39ኬጤያዊው ኦርዮ፤ ሁሉም በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።