ለኢየሩሳሌም ምእመናንስለሚደረግ አስተዋፅኦ
1ለቅዱሳን ስለሚደረገው አስተዋፅኦ በገላትያ ላሉት ምእመናን እንደ ደነገግሁት እናንተም እንዲሁ አድርጉ። 2እኔ ስመጣ ይህ የገንዘብ ማዋጣት ያንጊዜ እንዳይሆን፥ ከእናንተ ሰው ሁሉ በየሳምንቱ እሑድ የተቻለውን ያወጣጣ፤ ያገኘውንም በቤቱ ይጠብቅ። 3በመጣሁ ጊዜም ስጦታችሁን ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሱ ዘንድ የመረጣችኋቸውን ሰዎች መልእክቴን ጨምሬ እልካቸዋለሁ። 4ለመሄድ ቢቻለኝ ግን እኔ ራሴ እሄዳለሁና፥ እነርሱም አብረውኝ ይሄዳሉ። 5መቄዶንያም ደርሼ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመቄዶንያ በኩል አልፋለሁና። 6እናንተም ወደምሄድበት ትሸኙኝ ዘንድ ምንአልባት የሆነውን ቀን ያህል በእናንተ ዘንድ እቈይ፥ ወይም እከርም ይሆናል። 7አሁን እግረ መንገዴን ላያችሁ አልሻም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የፈቀደ እንደ ሆነ የሆነውን ቀን ያህል በእናንተ ዘንድ እንደምቈይ ተስፋ አደርጋለሁ። 8እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ። 9ሥራ የሞላበት ታላቅ በር ተከፍቶልኛልና፤ ነገር ግን ብዙዎች ተቃዋሚዎች አሉ። 10ጢሞቴዎስም በመጣ ጊዜ በእናንተ ዘንድ ያለ ፍርሀት እንዲኖር ተጠንቀቁ፤ እንደ እኔ የእግዚአብሔርን ሥራ ይሠራልና። 11የሚንቀውም አይኑር፤ ከወንድሞቻችን ጋር እጠብቀዋለሁና፥ ወደ እኔ እንዲመጣ በሰላም ሸኙት። 12ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስም ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ መላልሼ ማልጄው ነበር፤ አሁን ሊመጣ አልወደደም፤ በተቻለው ጊዜ ግን ይመጣል። 13ትጉ፤ በሃይማኖትም ቁሙ፤ ታገሡ ጽኑ፤ 14ሁሉን በፍቅር አድርጉ። 15ወንድሞቻችን ሆይ፥ የእስጢፋኖስና የፈርዶናጥስ፥ የአካይቆስም ቤተሰቦች፥ የአካይያ መጀመሪያዎች እንደ ሆኑ፥ ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቁ ዘንድ እማልዳችኋለሁ። 16እናንተም እንደ እነዚህ ላሉትና ከእኛ ጋር በሥራ ተባብሮ ለሚደክም ሁሉ ትታዘዙላቸው ዘንድ እማልዳችኋለሁ። 17እስጢፋኖስ፥ ፈርዶናጥስና አካይቆስ በመምጣታቸውም ደስ ይለኛል፤ እናንተ ያጐደላችሁትን እነርሱ ፈጽመዋልና። 18እነርሱ መንፈሴንና መንፈሳችሁን ደስ አሰኝተዋል፤ እንዲህ ያሉትንም ዕወቋቸው። 19በእስያ ያሉ ምእመናን ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ አቂላና ጵርስቅላ በቤታቸው ከእነርሱ ጋር ያሉ ምእመናንም ሁሉ በጌታችን እጅግ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 20ወንድሞቻችሁ ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል፤ በተቀደሰች ሰላምታ እርስ በርሳችሁ ሰላም ተባባሉ። 21እኔ ጳውሎስ ይህን ሰላምታ በእጄ ጻፍሁ። 22ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወደው የተለየ ይሁን፤ ጌታችን ይመጣል። 23የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን። 24የእኔም ፍቅር በኢየሱስ ክርስቶስ ከእናንተ ጋር ይሁን። አሜን።