1አቤሜሌክም ኤርምያስ ከላከው ቦታ በቀትር ጊዜ በለሱን አመጣ፤ ጽፍቅ ያለች ዱርንም አገኘ፤ ጥቂትም ያርፍ ዘንድ በጥላዋ ስር ተቀመጠ፤ በለስ ያለባትንም ሙዳይ ተንተርሶ ስድሳ ስድስት ዓመት ተኛ፤ ከመኝታውም አልነቃም። 2ከዚያም ዘመን በኋላ ከመኝታው ነቅቶ ተነሣ፤ “ገና ራሴን ይከብደኛልና፥ እንቅልፌንም አልጨረስሁምና ዳግመኛ ጥቂት ልተኛ” አለ። 3ያንም የበለሱን ሙዳይ ከፈተ፤ በለሶችም አዲስ ሆነው፥ ወተታቸውም ሲፈስስ አገኘ፤ ራሱንም ከብዶት ነበርና እንቅልፉንም አልጨረሰምና ይተኛ ዘንድ ወደደ። 4እንዲህም አለ፥ “ተመልሼ እንዳልተኛ እንዳልዘገይም እፈራለሁ፤ አባቴ ኤርምያስ ተግቶ በጧት ልኮኛልና እንዳይቈጣኝ እፈራለሁ። 5ሙቀት ሆኗልና፥ በሁሉም የሚተውበት ጊዜ የለምና አሁን ተነሥቼ እሄዳለሁ።” 6ተነሥቶም የበለሱን ሙዳይ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ገባ። ከተማውንም ቤቱንም አላወቀም። 7ጽኑ ድንጋጤ መጥቶበታልና “አቤቱ፥ አንተ የተመሰገንህ ነህ” አለ። 8እንዲህም አለ፥ “ይህቺ ከተማ ኢየሩሳሌም አይደለችምን? በተራራው ጎዳና መጥቻለሁና፥ ራሴንም ከብዶኛልና፥ እንቅልፌንም አልጨረስሁምና አእምሮዬን ዘንግቼ ምናልባት ተስቶኝ ይሆን? 9ከተማዪቱ ባዕድ እንደ ሆነችብኝ በኤርምያስ ዘንድ ይህን ነገር እንዴት እናገራለሁ?” ኢየሩሳሌምም እንደ ሆነች በከተማው ያለውን ምልክት ሁሉ ፈለገ። 10ዳግመኛም ወደ ከተማ ተመለሰ፤ የሚያውቀውም እንዳለ ፈለገ፤ ነገር ግን አላገኘም፤ “ታላቅ ድንጋጤ በእኔ መጥቶብኛልና አቤቱ፥ አንተ የተመሰገንህ ነህ” አለ። 11ሁለተኛም ከከተማ ርቆ ወጣ፤ እያዘነም ተቀመጠ፤ ሲሄድም አያውቅም ነበር፤ የበለሱንም ሙዳይ አኖረ፤ “ይህን ድንቁርና እግዚአብሔር ከእኔ እስኪያርቅልኝ ድረስ በዚህ እቀመጣለሁ” አለ። 12ከዚህ በኋላ ተቀምጦ ሳለ አንድ ሽማግሌ ሰው ከምድረ በዳ ሲመለስ አየ። 13አቤሜሌክም እንዲህ አለ፥ “አንተ ሽማግሌ፥ ይቺ ከተማ ማን ናት? ብዬ እጠይቅሃለሁ።” 14ያም ሽማግሌ፥ “ኢየሩሳሌም ናት” አለው፤ “ያገኘሁት ሰው የለምና የእግዚአብሔር ካህን ኤርምያስ ወዴት አለ? ሌዋዊው ባሮክና የከተማው ሕዝብ ሁሉስ ወዴት አሉ?” አለው፤ 15ሽማግሌውም እንዲህ አለው፥ “አንተ ከዚች ከተማ አይደለህምን? ይህን ያህል ዘመን ኖረህ የእርሱን ነገር ትጠይቅ ዘንድ ኤርምያስን ዛሬ ማን ዐሰበው? 16ተማርኮ በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ ተሰጥቶአልና፤ እስራኤልንም ያስተምር ዘንድ ወደ ባቢሎን ሄዶአልና ኤርምያስስ ከሕዝቡ ጋር በባቢሎን አለ።” 17አቤሜሌክም ያንጊዜ ከዚያ ከሽማግሌው ይህን ቃል ሰማ። 18አቤሜሌክም እንዲህ አለው፥ “ሰውን፥ ይልቁንም ሽማግሌውን ሰው ሊንቁት አይገባም እንጂ አንተ ሽማግሌ ሰው ባትሆን በሰደብሁህ ነበር፤ በአንተም በዘበትሁብህ ነበር፤ ያም ባይሆን አእምሮውን ያጣ ሽማግሌ ብዬ በሰደብሁህ ነበር። 19ሕዝቡ ተማርከው ወደ ባቢሎን ሄዱ፤ ስለምትለውስ ነገር የሰማይ ሻሻቴ እንኳ በእነርሱ ላይ ቢወርድ ወደ ባቢሎን ተማርከው ይሄዱ ዘንድ ጊዜው አይደለም። 20አንተ ግን ተማርከው ወደ ባቢሎን ሄዱ ትላለህ፤ በሕዝቡ ዘንድ ላሉ ለበሽተኞች እንሰጥ ዘንድ አባቴ ኤርምያስ እኔን እንደ ላከኝ ጥቂት በለስ ላመጣ ወደ አግሪጳስ ወይን ቦታ ሄድሁ። 21ሄጄም ከዚያ ደረስሁ፤ ያዘዘኝንም ይዤ ተመለስሁ፤ ስሄድም አንዲት ዛፍ አገኘሁ፤ የቀትር ጊዜ ነበርና በበታችዋ ዐርፍ ዘንድ ተቀመጥሁ። 22ከዚያም የበለሱን ሙዳይ ተንተርሼ ተኛሁ፤ ከእንቅልፌም በነቃሁ ጊዜ የዘገየሁ መሰለኝ፤ የበለሱንም ሙዳይ ከፍቼ አየሁ፤ መርጬ እንደለቀምኋቸው ወተቱ ሲፈስስ አገኘሁት። 23እነሆ፥ አንተ ሕዝቡ ተማርከው ወደ ባቢሎን ሄዱ ትላለህ፤ እነሆ፥ በለሱ እንዳልጠወለገ እይ” ብሎ የበለሱን ሙዳይ ከፍቶ አሳየው። 24ሽማግሌውም በለሱ አዲስ እንደ ሆነ፥ ወተቱም እንደሚፈስስ አየ፤ ያንጊዜም ሽማግሌው አደነቀ። 25አቤሜሌክንም እንዲህ አለው፥ “ልጄ፥ አንተ ደግ ሰው ነህ፤ ፈጣሪህ የዚህችን ከተማ ጥፋት ሊያሳይህ አልወደደምና አምላክ ለአንተ መረጋጋትን አምጥቶ አድኖሃል። 26እነሆ፥ ሕዝቡ ወደ ባቢሎን ተማርከው ከሄዱ ዛሬ ስድሳ ስድስት ዓመት ሆነ። 27ልጄ፥ ፈጽመህ ልታውቅስ ከወደድህ ዘሮችዋ እንደ በቀሉ ወደ እርሻዎች ፈጽመህ ተመልከት፤ የበለስም ጊዜው አይደለም፤” ያንጊዜ አቤሜሌክ የዚህ ሁሉ ጊዜው እንዳልሆነ ዐወቀ። 28ቃሉንም አሰምቶ፥ “የሰማይና የምድር አምላክ፥ በሀገሩ ሁሉ ያሉ የጻድቃን ነፍሳት ዕረፍታቸው የሆንህ ጌታዬና አምላኬ ሆይ፥ አመሰግንሃለሁ፥” አለ። 29ሽማግሌውንም፥ “ይህ ወር ምንድን ነው?” አለው፤ እርሱም፦ የኔሳን ወር ዐሥራ ሁለተኛው ቀን፥ ይኸውም ሚያዝያ ነው” አለው። 30ከዚህም በኋላ አቤሜሌክ ለዚህ ሽማግሌ ከበለሶቹ ሰጠው፤ እርሱም፥ “አምላክ ወደ ሰማያዊት ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ይምራህ” አለው።