ተረፈ ባሮክ
1ኤርምያስም ጳስኮርን እንዲህ አለው፥ “እናንተስ በዘመናችሁ ሁሉ ከአባቶቻችሁና ከእናንተ በኋላ ከሚመጡ ልጆቻችሁ ጋር ጽድቅን ትቃረኗታላችሁ። 2እነርሱስ ከአባቶቻችሁ ይልቅ እጅግ የተናቀች ኀጢአትን ሠሩ። እነርሱም ዋጋ የማይገኝለትን ይሸጡታል፤ ሕማማትን የሚያስወግደውን እንዲታመም ያደርጉታል፤ ኀጢአትን የሚያስተሰርየውንም ይፈርዱበታል። 3የእስራኤል ልጆች የተስማሙበትን የክቡሩን ዋጋ ሠላሳ ብር ይቀበላሉ፤ ያንም ብር ለሸክላ ሠሪ ቦታ ዋጋ አድርገው ይሰጡታል። 4እዚአብሔርም እንዳዘዘኝ እንዲሁ እናገራለሁ። 5ስለዚህ ንጹሕ ደምን ፈርደው አፍስሰዋልና ፍርድና ጥፋት በእነርሱ ላይ፥ ከእነርሱም በኋላ በልጆቻቸው ላይ ይወርድባቸዋል፤” 6ወደ ባቢሎን በተማረኩ ጊዜ ስውር ያልሆነ ባሮክ ከተናገረው ነገር የቀረ ይህ ነው። 7እንዲህም ሆነ፤ የከለዳውያን ንጉሥ የእስራኤልን ልጆች በማረካቸው ጊዜ እግዚአብሔር ኤርምያስን ተናገረው። 8እንዲህም አለው፥ “ወዳጄ ኤርምያስ ሆይ፥ ከዚህች ከተማ ውጣ፤ ከሚኖሩባት ሰዎች ኀጢአት ብዛት የተነሣ አጠፋታለሁና አንተና ባሮክ ውጡ። 9ልመናህ በከተማዪቱ መካከል እንደ ጽኑ ምሰሶ፥ በዙሪያዋም እንደ አድማስ ቅጥር ነውና፤ አሁንም የከለዳውያን ሠራዊት ሳይመጣና ሀገሪቱን ሳይከባት ተነሥታችሁ ሂዱ፥ ውጡም።” 10ኤርምያስም እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ እለምንሃለሁ፤ በፊትህ ይናገር ዘንድ ባሪያህን እዘዘው።” 11እግዚአብሔርም፥ “ወዳጄ ኤርምያስ ሆይ! ተናገር” አለው። 12ኤርምያስም እንዲህ ሲል ተናገረ፥ “ሁሉን የምትገዛ አቤቱ፥ ንጉሡ ከሠራዊቱ ጋር ይታበይና በአምላክ ከተማ በረታሁባት ይል ዘንድ የመረጥኻትን ይህቺን ከተማ በከለዳውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? 13አቤቱ፥ ይህ አይሁን፤ ከወደድህም በእጅህ አጥፋት።” 14እግዚአብሔርም ኤርምያስን አለው፥ “በሚኖሩባት ሰዎች ኀጢአት አጠፋታለሁና አንተ ወዳጄ ስለ ሆንህ ባሮክና አንተ ተነሥታችሁ ውጡ። 15እኔ አስቀድሜ በሮችዋን ካልከፈትሁ ንጉሡና ሠራዊቱ ወደ ሀገሪቱ መግባት አይቻላቸውም። 16አሁንም ተነሥተህ ወደ ባሮክ ሂድ፤ ይህንም ነገር ሁሉ ንገረው፤ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ተነሥታችሁ ወደ ከተማዪቱ ቅጥር ኑ። 17እኔ አሳያችኋለሁ፤ እኔም አስቀድሜ ከተማዪቱን ካላጠፋኋት ወደ እርስዋ መግባት አይችሉም።” 18ጌታም ይህን ተናግሮ ከኤርምያስ ዘንድ ሄደ። 19ያንጊዜም ኤርምያስ ልብሱን ቀደደ፤ በራሱም ላይ ትቢያ ነሰነሰ፤ ወደ ቤተ መቅደስም ገባ። 20ባሮክም ኤርምያስን በራሱ ላይ ትቢያ ነስንሶ፥ ልብሶቹንም ቀድዶ ባየው ጊዜ፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ሆንህ? ሕዝቡስ ምን ኀጢአት ሠሩ?” ብሎ ቃሉን አሰምቶ ጮኸ። 21ሕዝቡ በሳቱ ጊዜ ኤርምያስ ያዝን ነበርና፥ በራሱም ትቢያ ይነሰንስ ነበርና፥ የሕዝቡም በደላቸው እስኪሰረይላቸው ድረስ ለሕዝቡ ይጸልይላቸው ነበርና። 22ባሮክም፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ሆንህ?” ብሎ ጠየቀው። ኤርምያስም እንዲህ አለው፥ “ልቡናችንን እንቅደድ እንጂ ልብሶቻችንን እንዳንቀድ ተጠበቅ” አለው። 23“ከዛሬ ጀምሮ እነዚህን ወገኖች ይቅር አይሏቸውምና እንባን እስክንመላቸው ድረስ በሚገባ እናለቅስ ዘንድ ወደ ጕድጓዶች ውኃን አንጨምር” አለው። 24ባሮክም፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ሆንህ?” አለ። 25ኤርምያስም፥ “አምላክ ከተማዋን በከላውዴዎን ንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፥ ሕዝቡንም በክፉ ነገር ይማርካቸዋልና ነው፤” አለው። 26ባሮክም ይህን ሁሉ ነገር ሰምቶ ልብሶቹን ቀደደና፥ “አባቴ ኤርምያስ ሆይ፥ ምን ላኩብህ?” አለው። 27ኤርምያስም፥ “ነገሩን በእውነት ታውቅ ዘንድ ከሌሊቱ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ከእኔ ጋር ቈይ” አለው። 28በቤተ መቅደስም እያለቀሱ ተቀመጡ፤ ከሌሊቱም ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ኤርምያስን ይወጣ ዘንድ ነገረው። 29ከባሮክም ጋር ወጣ፤ ወደ ቅጽሩም ደረሱ፤ እየጸለዩም ተቀመጡ። 30የመለከት ድምፅም ተሰማ፤ መላእክትም ከሰማያት መጡ፤ በእጃቸውም የእሳት መብራት ይዘው በቅጥሯ ቆመው ነበር።