እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ መረጠ
1በክርስቶስ እውነት እነግራችኋለሁ፤ ሐሰትም አልናገርም። ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልናል፤ 2በጊዜው ሁሉ ብዙ ኀዘን፥ የማያቋርጥም ጭንቀት በልቤ አለ። 3በሥጋ ዘመዶችና ወንድሞች ስለሚሆኑ እኔ ከክርስቶስ እለይ ዘንድ እጸልያለሁ። 4እናህም ልጅነት፥ ክብር፥ ኪዳን፥ ሕግና አምልኮ ያላቸው፥ ተስፋም የተሰጣቸው እስራኤላውያን ናቸው። 5እነርሱም አባቶቻችን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን። 6ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል አይታበልም፤ እስራኤል ሁሉ እስራኤላውያን አይደሉምና። 7የአብርሃም ዘር ሁሉ ልጆቹ የሆኑት አይደለም፤ ከይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል አለው እንጂ። 8ልጆች እንዲሆኑት ተስፋ ያናገረለት የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፤ እነዚህ ከሥጋ የተወለዱ ግን የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም። 9“ከርሞ እንደ ዛሬ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ታገናለች፤” ብሎ ተስፋ ሰጥቶታልና። 10ነገር ግን ለእርስዋ ብቻ አይደለም፤ ርብቃም ለአባታችን ለይስሐቅ መንታ በፀነሰች ጊዜ፥ 11ሳይወለዱ፥ ክፉና መልካም ሥራም ሳይሠሩ የእግዚአብሔር መምረጡ በምን እንደ ሆነ ይታወቅ ዘንድ፥ 12እርሱ የጠራው ነው እንጂ ሰው በሥራው የሚመረጥ አንዳይደለም ያውቁ ዘንድ፥ ለርብቃ፥ “ታላቁ ለታናሹ ይገዛል” አላት። 13“ያዕቆብን ወደድሁ፤ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንዲሁ ተጽፎአልና። 14እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያደላልን? አያደላም። 15እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፥ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ይቅር የምለውንም ይቅር እለዋለሁ።” 16አሁንም ለሮጠና ለቀደመ አይደለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ላለው ነው እንጂ። 17እግዚአብሔርም ለፈርዖን በመጽሐፍ እንዲህ አለው፥ “ኀይሌን በአንተ ላይ እገልጥ ዘንድ፥ ስሜም በምድር ሁሉ ይሰማ ዘንድ ስለዚህ አስነሣሁህ።” 18እነሆ፥ የሚወድደውን ይምረዋል፤ የሚወድደውንም ልቡን ያጸናዋል። 19እንግዲህ ምን ትላለህ? አንተ እግዚአብሔርን ትነቅፈዋለህን? ምክሩንስ የሚቃወማት አለን?። 20ሰው ሆይ፥ እግዚአብሔርን የምትከራከረው አንተ ምንድን ነህ? ሥራ ሠሪውን እንዲህ አታድርገኝ ሊለው ይችላልን? 21ሸክላ ሠሪ ከአንድ ጭቃ ግማሹን ለክብር፥ ግማሹንም ለኀሳር አድርጎ ዕቃን ሊሠራ አይችልምን? 22እግዚአብሔርም ኀይሉን የሚገልጽበትን ቅጣቱን ሊያሳይ ቢወድ፥ ትዕግሥቱን ካሳየ በኋላ ለማጥፋት የተዘጋጁትን ቍጣውን የሚገልጽባቸውን መላእክት ያመጣል። 23ዳግመናም የክብሩን ባለጠግነት ሊያሳይ ቢወድ አስቀድሞ ለወደዳቸውና ለጠራቸው ለይቅርታ የተዘጋጁ የምሕረት መላእክትን ያመጣል። 24ወደ ክብሩ የጠራንና የሰበሰበንም እና ነን፤ ነገር ግን ከአሕዛብም ነው እንጂ ከአይሁድ ብቻ አይደለም። 25ነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ እንዳለ “ወገኔ ያልነበረውን ወገኔ አደርገዋለሁ፤ ወዳጄ ያልነበረችውንም ወዳጄ አደርጋታለሁ። 26የእግዚአብሔር ወገኖች አይደላችሁም ይባሉ በነበሩበት ሀገርም የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ።” 27ኢሳይያስም ድምፁን ከፍ አድርጎ ስለ እስራኤል እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል ልጆች ቍጥራቸው እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም የተረፉት ይድናሉ። 28እግዚአብሔር በዓለም ውስጥ ያደርገው ዘንድ ያለውን ያለቀና የተቈረጠ ነገርን ይናገራልና።” 29ኢሳይያስም አስቀድሞ እንደ ተናገረ “እግዚአብሔር ጸባኦት ዘር ያስቀረልን ባይሆን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፥ ገሞራንም በመሰልን ነበር።”