የአብርሃም ምሳሌነት
1እንግዲህ በሥጋ የቀድሞ አባታችን የሆነው አብርሃም ምን አገኘ እንላለን? ይህን በሥራው አግኝቶአልን? 2አብርሃም በሥራው ጸድቆስ ቢሆን ትምክሕት በሆነው ነበር፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም። 3መጽሐፍስ ምን ይላል? አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት። 4ለሚሠራ ዋጋው እንደሚገባው እንጂ በለጋስነት እንደ ሰጡት ሆኖ አይቈጠርበትም። 5ለማይሠራ ግን ኀጢአተናውን በሚያጸድቀው ካመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቈጠርለታል። 6የኦሪትን ሥራ ሳይፈጽም ማመኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅ ሆኖ የሚቈጠርለትን ሰው ዳዊት “ብፁዕ” በሚልበት አንቀጽ እንዲህ ይላል፦ 7“መተላለፋቸው የቀረላቸው፥ ኀጢአታቸውም የተሰረየላቸው ብፁዓን ናቸው። 8እግዚአብሔርም በደሉን የማይቈጥርበት ሰው ብፁዕ ነው።” 9እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገዘር ተነገረን? ወይስ ስለ አለመገዘር? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት እንላለንና። 10ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ተገዝሮ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገዘር? ሳይገዘር ነው እንጂ ተገዝሮ ሳለ አይደለም። 11ሳይገዘር እግዚአብሔር አብርሃምን በእምነት እንደ አጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን የጽድቅ ማኅተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው። ሳይገዘሩ ለሚያምኑ ሁሉ አባት ሊሆን፥ አብርሃም በእምነት እንደ ከበረ እነርሱም በእምነት እንደሚከብሩ ያውቁ ዘንድ ሰጠው። 12ለተገዘሩትም አባት ይሆን ዘንድ ነው፤ ነገር ግን ለተገዘሩት ብቻ አይደለም፤ እርሱ አባታችን አብርሃም ሳይገዘር እንደ አመነ ሳይገዘሩ የአባታችን የአብርሃምን የሃይማኖቱን ፍለጋ ለሚከተሉ ደግሞ ነው እንጂ።
ስለ አብርሃምና ስለ ዘሩ ተስፋ
13አብርሃም፥ ዘሩም ዓለምን ይወርስ ዘንድ ተስፋ ያገኘ የኦሪትን ሥራ በመሥራት አይደለም፤ በእግዚአብሔር ቃል፥ እርሱንም በማመን በእውነተና ሃይማኖቱ ይህን አገኘ እንጂ። 14የኦሪትን ሕግ የፈጸመ ብቻ ተስፋ የሚያገኝ፥ ዓለምንም የሚወርስ ቢሆን ኖሮ፥ ለአብርሃም እምነቱ ባልጠቀመውም ነበር፤ ተስፋውንም ባላገኘም ነበር። 15የኦሪት ሕግ በአፍራሹ ላይ ቅጣትን ያመጣልና፤ የኦሪት ሕግም ከሌለ መተላለፍ የለም። 16ስለዚህም እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠው ተስፋ የታመነ ይሆን ዘንድ፥ የሚጸድቁ በእምነት እንጂ የኦሪትን ሥራ በመፈጸም ብቻ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ እግዚአብሔር ጽድቅን በእምነት አደረገ። 17“ለብዙዎች አሕዛብ አባት አደርግሃለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈ ሙታንን በሚያስነሣቸው፥ የሌሉትንም እንደ አሉ በሚያደርጋቸው በአመነበት በእግዚአብሔር ፊት አብርሃም የሁላችን አባት ነው። 18አብርሃም “ዘርህ እንዲሁ ይሆናል” ብሎ እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠው ተስፋ ባልነበረ ጊዜ የብዙዎች አሕዛብ አባት እንደሚሆን አመነ። 19አብርሃም የመቶ ዓመት ሽማግሌ ስለሆነ እንደ ምውት የሆነውን የራሱን ሥጋና የሣራ ማኅፀን ምውት መሆኑን እያየ በእምነት አልተጠራጠረም። 20እግዚአብሔር ያናገረለትንም ተስፋ ይቀራል ብሎ አልተጠራጠረም፤ በእምነት ጸና እንጂ፤ ለእግዚአብሔርም ክብርን ሰጠ። 21እግዚአብሔርም የሰጠውን ተስፋ ሊያደርግለት እንደሚችል በፍጹም ልቡ አመነ። 22ስለዚህም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት። 23ነገር ግን “ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” የሚለው ቃል የተጻፈ ስለ እርሱ ብቻ አይደለም። 24ስለ ኀጢአታችን የተሰቀለውን፥ ሊያስነሣንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ በአስነሣው ስለምናምን ስለ እናም ነው እንጂ።