የእግዚአብሔር ዙፋንና ሰማያዊው የጸሎት ሥነ ሥርዐት
1ከዚያ በኋላም አየሁ፤ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ “ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ፤” አለ። 2ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም ዙፋን በሰማይ ቆሞአል፤ በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤ 3ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ። 4በዙፋኑ ዙሪያም ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር። 5ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጣል፤ በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር፤ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው። 6በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዐይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ። 7ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፤ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፤ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፤ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል። 8አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፤ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዐይኖች ሞልተውባቸዋል፤