በአምባላይ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ፈረሰኛ
11ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም አምባላይ ፈረስ፤ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፤ በጽድቅም ይፈርዳል፤ ይዋጋልም። 12ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፤ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፤ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤ 13በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፤ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል። 14በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር። 15አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል። 16በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት “የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ” የሚል ስም አለው። 17አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፤ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ “መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ የብርቱዎችንም ሥጋ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር እራት ተከማቹ፤” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 19በፈረሱም የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ። 20አውሬውም ተያዘ፤ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ። 21የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።