ሁለቱ ምስክሮች
1በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፤ እንዲህም ተባልሁ “ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ። 2በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው፤ አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል። 3ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።” 4እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው። 5ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፤ ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። 6እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፤ ውሕሃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው። 7ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል፤ ያሸንፋቸውማል፤ ይገድላቸውማል። 8በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል፤ እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። 9ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፤ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። 10እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስላሠቃዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ በደስታም ይኖራሉ፤ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ። 11ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው፤ በእግሮቻቸውም ቆሙ፤ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። 12በሰማይም “ወደዚህ ውጡ” የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ። 13በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ከከተማይቱም ዐሥረኛው እጅ ወደቀ፤ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፤ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፤ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ። 14ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል።