የመዓርግ መዝሙር።
1አቤቱ ዳዊትን ገርነቱንም ዅሉ ዐስብ 2ለእግዚአብሔር እንደ ማለ ለያዕቆብም አምላክ እንደ ተሳለ 3በእውነት ወደቤቴ ድንኳን አልገባም ወደምንጣፌም ዐልጋ አልወጣም 4ለዐይኖቼም መኝታ ለሽፋሽፍቶቼም እንቅልፍ ለጕንጮቼም ዕረፍትን አልሰጥም 5ለእግዚአብሔር ስፍራ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እስካገኝ ድረስ ብሎ 6እንሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው 7ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን 8አቤቱ ወደ ዕረፍትኽ ተነሥ አንተና የመቅደስኽ ታቦት 9ካህናትኽ ጽድቅን ይልበሱ ቅዱሳንኽም ደስ ይበላቸው 10ስለ ዳዊት ስለ ባሪያኽ የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ 11እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ አይጸጸትምም እንዲህ ብሎ፦ከሆድኽ ፍሬ በዙፋንኽ ላይ አስቀም ጣለኹ 12ልጆችኽ ኪዳኔን ይህንም የማስተምራቸውን ምስክሬን ቢጠብቁ ልጆቻቸው ደግሞ በዙፋንኽ ላይ ለዘለዓ ለም ይቀመጣሉ 13እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ማደሪያውም ትኾነው ዘንድ ወዷ፟ታልና እንዲህ ብሎ፦ 14ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለኹና በዚች ዐድራለኹ 15አሮጊቶቿን እጅግ እባርካለኹ ድኻዎቿንም እንጀራ አጠግባለኹ 16ካህናቷንም ደኅንነትን አለብሳቸዋለኹ ቅዱሳኖቿም እጅግ ደስ ይላቸዋል 17በዚያ ለዳዊት ቀንድን አበቅላለኹ ለቀባኹትም ሰው መብራትን አዘጋጃለኹ 18ጠላቶችንም ዕፍረትን አለብሳቸዋለኹ በርሱ ግን ቅድስናዬ ያብባል