እግዚአብሔር ለባሮክ የነገረው ተስፋ
1በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመተ መንግሥት እነዚህን ቃላት ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፍ በጻፋቸው ጊዜ፥ ነቢዩ ኤርምያስ ለኔርዩ ልጅ ለባሮክ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 2“ባሮክ ሆይ! የእስራኤል አምላክ እግዚእብሔር እንዲህ ይልሃል፦ 3አንተ፦ እግዚአብሔር በሕማሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፤ ዕረፍትንም አላገኘሁም ብለሃል። 4እንዲህ በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የሠራሁትን አፈርሳለሁ፥ የተከልሁትንም እነቅላለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ ነው። 5ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ እነሆ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልጋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።”