የኤርምያስ መጠራት
4የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 5“በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።” 6እኔም፥ “ወዮልኝ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ ሕፃን ነኝና እናገር ዘንድ አልችልም” አልሁ። 7እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፥ “ወደምልክህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፥ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና፦ ሕፃን ነኝ አትበል። 8እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋራ ነኝና ከፊታቸው የተነሣ አትፍራ” ይላል እግዚአብሔር። 9እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰ፥ እግዚአብሔርም አለኝ፥ “እነሆ፥ ቃሌን በአፍህ ውስጥ አኑሬአለሁ፤ 10እነሆ ትነቅልና ታፈርስ ዘንድ፥ ታጠፋና ትገለብጥ ዘንድ፥ ትሠራና ትተክል ዘንድ በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾሜሃለሁ።” 11ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል፥ “ኤርምያስ ሆይ! ምን ታያለህ?” እያለ ወደ እኔ መጣ። እኔም፥ “የሎሚ በትር አያለሁ” አልሁ። 12እግዚአብሔርም፥ “የተናገርሁትን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና መልካም አይተሃል” አለኝ። 13ሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ምን ታያለህ?” እኔም፥ “የሚፈላ አፍላል አያለሁ፤ ፊቱም ወደ ሰሜን ወገን ነው” አልሁ። 14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ከሰሜን ወገን ክፉ ነገር በምድሪቱ በተቀመጡ ሁሉ ላይ ይፈስሳል። 15እነሆ እኔ በሰሜን ያሉትን የመንግሥታቱን ወገኖች ሁሉ እጠራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ እነርሱም ይመጣሉ እያንዳንዳቸውም በኢየሩሳሌም በር መግቢያ በዙሪያዋና በቅጥርዋ ሁሉ ላይ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ላይ ዙፋናቸውን ያስቀምጣሉ። 16ስለ ክፋታቸውም ሁሉ፥ እኔን ስለ ተዉ፥ ለሌሎችም አማልክት ስለ ሠዉ፥ ለእጃቸውም ሥራ ስለ ሰገዱ፥ ፍርዴን በእነርሱ ላይ እናገራለሁ። 17አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥም፤ ያዘዝሁህንም ሁሉ ንገራቸው፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትፍራ። በፊታቸውም አትደንግጥ አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ይላል እግዚአብሔር። 18እነሆ በምድሪቱ ሁሉ ላይ፥ በይሁዳም ነገሥታት በአለቆችዋና በካህናቷ ላይ፥ በምድሪቱም ሕዝብ ላይ እንደ ተመሸገች ከተማ፥ እንደ ብረትም ዓምድ፥ እንደ ናስም ቅጥር ዛሬ አድርጌሃለሁ። 19ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፤ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፥” ይላል እግዚአብሔር።